ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የጣሊያን ቆይታቸውን በማጠናቀቅ ዳቦስ ገቡ

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በጣሊያን የነበረውን ይፋዊ ጉብኝት በማጠናቀቅ በስዊዘርላንድ ዳቮስ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ዳቦስ ገብተዋል፡፡ 

የልዑካን ቡድኑ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቀነህ ገበየሁን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናትን ያካተተ ሲሆን ከጣሊያን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውጤታማ ውይይቶችን አካሂዷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተመራው የልዑካን ቡድኑ ከጣሊያን ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ እና ከጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፕ ኮንቴ ጋር ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን በሁሉም ዘርፍ አጠናክረው በሚቀጥሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ ውይይቶችን አድርጓል።

የጣሊያን መንግሥት በኢትዮጵያ የሚሠሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶቸን በገንዘብ ለመደገፍ ቃል መግባቱንም መሪዎቹ በጋራ በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አረጋግጠዋል። 

የጣሊያን መንግሥት ከአዲስ አበባ ምጽዋ ለሚገነባው የባቡር ሃዲድ ግንባታ ፕሮጀክት ጥናት ሙሉ ወጪውን ለመሸፈንም ቃል ገብቷል። በአዲስ አበባ የተማሪዎች ምገባ ለማካሄድ የሚያግዝ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ (የዳቦ ፋብሪካ) ለመገንባትም ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ከዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤዝሊ፣ ከዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆዜ ግራዚያኖ ድ ሲልቫ እና ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ፕሬዝዳንት ሮበርት ጊልበርት ጋር ድርጅቶቹ የልማት አጋርነታቸውን አጠናክረው በሚቀጥሉበት ዙሪያ ውጤታማ ውይይቶችን አድርገዋል።

በተጨማሪም ከሮማው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ ጋር፣ በቫቲካን የቅዱስ እስጢፋኖስ የአቢሲኒያ ቤተ ክርስቲያን ከካርዲናል አባ ብርሃነ ኢየሱስ ጋር እንዲሁም ከቫቲካን ዋና አስተዳዳሪ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ጋር ሁለቱ አገሮች የቆየ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን በመጠቀም የሕዝብ ለሕዝብ እና የባሕል ትስስሩን አጠናክረው መቀጠል ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ ውይይቶችን አድርገዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወቅርነህ ገበየሁ በበኩላቸው የጣሊያን ታዋቂ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በተዘጋጀው ፎረም ላይ በመገኘት ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።

ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በተመለከተ ያላቸውን ተሞክሮና ምስክርነት ሰጥተዋል።

የልዑካን ቡድኑ የጣሉያን ቆይታውን በይፋ በማጠናቀቅ በስዊዘርላንድ ዳቮስ በሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ለመሳተፍ ዛሬ ዳቦስ ገብተዋል።

ፎረሙ ‹‹መፃዒ ዕድላችንን በጋራ እንወሰን›› በሚል መሪ ሐሳብ በርካታ የዓለም መሪዎችን ጨምሮ፣ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መስራቾችና ባለሀብቶች፣ ‹ቲንክኮች›፣ የሙያው ጠበብቶች እና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ይሳተፉበታል፤ ከ3000 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ዛሬው በይፋእንደሚከፈትም ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በፎረሙ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
(ምንጭ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት)