“መደመር ያለፈ ፀጋችንን እንደገና የመፈተሽና ወደ ብልጽግና የመመለስ መርኅ ነው “-ዶክተር አብይ አህመድ

መደመር ያለፈ ፀጋችንን እንደገና የመፈተሽና ወደ ብልጽግና የመመለሻ መርኅ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዳቦስ ኢኮኖሚክ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግራቸው በሀገሪቱ ስለተጀመሩት ለውጦች ዳሰሳ አድርገዋል፡፡

ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሕገ-መንግሥታዊ ቃል-ኪዳንን ለማክበር እየሠሩ መሆናቸውን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸውን፣ በግዞት የነበሩ ፖለቲከኞችንና መገናኛ ብዙኃንን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

በምጣኔ ሀብት ዘርፉ ኢትዮጵያን የዓለም ምጣኔ ሀብት ማዕከል እንድትሆን እየሠሩ መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምጣኔ ሀብት ሥርዓት እየዘረጋን ነው ብለዋል፡፡

“ሴቶች በሀገራችን ዋና ዋና የሚኒስትር ቦታዎች ላይ ተሰይመዋል፤ የፆታ ስብጥርንም አመጣጥነናል፤ በዘመናዊት ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሴት ርዕሰ ብሔር መርጠናል፤ ግን ይህ በቂ አይደለም” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የ100 ሚሊዮኖች ሀገር ኢትዮጵያ አሁንም ወጣትና አምራች ዜጎቿን ያላረካች በመሆኑ በትምህርትና መሠል የሰብዓዊ ልማቶች ላይ በትኩረት ልንሠራ እየተዘጋጀን ነው ሲሉም ለፎረሙ ተሳፊዎች ገልጸዋል፡፡

ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መነቃቃት ትኩረት እንደሚሠጥ የገለጹት ዶክተር አብይ ‹‹ኢትዮጵያ አሁን በመሠረታዊ ተቋማዊ ለውጥ ውስጥ መሆኗንና ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግም እየተሠራ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

የግሉን ዘርፍ በግዙፍ መንግሥታዊ ተቋማት በሆኑ በቴሌኮም፣ በኃይል፣ በባቡርና በኢንዱስትሪ ፓርኮች የግል ባለሀብቶችን ለማሳተፍ እየጣርን ነው›› ብለዋል፡፡ 

‹የፐብሊክ-ፕራይቬት› ግንኙነትን ለማሻሻል የተጀመሩ ለውጦችንም በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ይህም ፈጣን ሀገራዊ ዕድገት እንድናስመዘግብና የበለጸገች ኢትዮጵያን እንድንፈጥር እንደሚያስችለን እናምናለን፡፡ የቢዝነስና የመንግሥት መስተጋብር ግልጽና አሳታፊ እንዲሆን እየሠራን ነው›› ነው ያሉት፡፡

ቀጠናዊ ውህደትና ለዓለም ክፍት መሆንንም እንደ መርህ እየተከተሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ታሪክ ከቀጠናዊ ውህደት በሰላምና በምጣኔ ሀብት ተጠቃሚ እንደምንሆን አስተምሮናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጎረቤት ሀገራት ጋር አብሮ መልማትን እንደሚያስቀድሙም ተናግረዋል፡፡

እንደ ሀገር ‹ሩቅ ለመጓዝ በጋራ፤ በፍጥነት ለመጓዝ በግል ሂድ› የሚለውን ሐሳብ እንከተላለን፡፡ ከጎረቤቶቻችን ጋር ሩቅ መጓዝ ደግሞ የበለጠ ይጠቅመናል›› ነው ያሉት ዶክተር ዐብይ በንግግራቸው፡፡
የጀመርናቸውን ለውጦች ለማጠናከር ለባለሀብቶች መተማመኛ መፍጠር እንዳለብን እናውቃለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ አዲስና ታላቅ ሕልም መሰነቋን ነው ለፎረሙ ተሳታፊዎች የገለጹት፡፡ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ገበያውን ለመክፈት መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

ያለፉት ዘጠኝ ወራት አካሄዳችን ደግሞ ትልቅ ተስፋ ያስጨበጠን ሆኗል፤ ኢትዮጵያውያን ለሩጫ የተፈጠርን ጎበዞችና ጠንካሮች ነን፤ እስከ ቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በአማካይ ከ8 በመቶ በላይ ዕድገት በማስመዝገብ ፈጣን የዓለማችን ሀገር ለመሆን እየሮጥን ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ስለነበረው አሁን ስላለው ሀገራዊ ሁኔታ ሲናገሩም ከዘጠኝ ወራት በፊት ቁልቁል ስትምዘገዘግ የነበረች ሀገር ነች፤ በወሰድነው ፖለቲካዊ እርምጃ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተደርጎ ለውጥ መጥቷል፤ አሁን ሀገራችን ላይ ትልቅ ተስፋ አለ፤ በሁሉም መስክ እያንሰራራች ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚነስትሩ በንግግራቸው አክለዋል፡፡