ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ጆን-ክላውድ ጀንከር ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቤልጂየም ብራሰልስ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ጆን-ክላውድ ጀንከር ጋር በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ በተመለከተ ገለፃም አድርገዋል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ጆን-ክላውድ ጀንከር በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ አድንቀው የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ወገኖችን ውይይት ተከትሎ 130 ሚሊዮን ዮሮ የሚያወጡ ሶስት የፋይናንስ ስምምነቶች ተፈርመዋል፡፡

የፋይናንስ ስምምነቱም በኢትዮጵያ ዘላቂ ኃይል ለማመንጨት ለተያዙ ፕሮጀክቶች፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና የሥራ እድል ፈጠራ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ እንደሚውል በስምምነቱ ተገልጿል።

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ዋነኛ የልማት አጋር ነው። (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)