አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ በባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረቡ

በጥረት ኮርፖሬት ተፈጽሟል ከተባለ የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ ዛሬ የባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

የክልሉ ፀረ ሙስና መርማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ይፈቀድልኝ በማለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅደዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው መርማሪ በእነሱ ላይ ያሉ መረጃዎችን 90 በመቶ መሰብሰቡን ጠቅሰው የጠየቀው የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድለት አይገባም በሚል ተከራክረዋል።

መርማሪ በበኩሉ 90 በመቶ መረጃ የተሰበሰበው በአምስት ኩባንያዎች ላይ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

በተጨማሪም መረጃው በተበታተነ መልኩ ስለሆነ የተሰበሰበውን ለማደራጀት ጊዜ ያስፈልገኛል ብሏል።

ከጠበቃ ጋር በተያያዘም አቶ በረከት ለፍርድ ቤቱ ገቢያቸው አነስተኛ መሆኑን እና በጡረታ ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ ቤተሰባቸውን አማክረው ጠበቃ እንድሚቀጥሩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

አቶ ታደሰ ካሳ በበኩላቸው በግላቸው መከራከር እንደሚችሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው ይከታተሉ ዘንድ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ መኖሪያቸው አዲስ አበባ መሆኑን በመጥቀስ ጉዳያቸው አዲስ አበባ እንዲታይላቸውም ነው የጠየቁት።

ሆኖም ጉዳዩ በክልሉ ከሚገኘው ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው በዚሁ ነው የሚታው ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም መርማሪዎች ተጠርጣሪዎቹ ካላቸው ተጽዕኖ ፈጣሪነት አንጻር ቢወጡ ሰነዶችን ሊያሸሹ እና ምስክሮች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ በማለት ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።

የግራ ቀኙን ያደመጠው ፍርድ ቤትም በአቃቤ ህግ የተጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡ (ኤፍ.ቢ. ሲ)