በሱማሌ ክልል በደረሰው የሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ 46 ሰዎች ተለይተዋል-የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ

በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በደረሰው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ 46 ሰዎች መለየታቸውን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል፡፡

ከተጠረጠሩት 46 ሰዎች ውስጥ 6ቱ የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ሌሎች የተቀሩት በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ተደብቀው እንዳሉ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የህዝብ  ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዝናቡ  ቱኑ  በዛሬው  ዕለት  በሠጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ወደ ሌሎች አገራት የኮበለሉትን ተጠርጣሪዎች የሚገኙበት   አገራት የተለዩ መሆኑንና መንግስት ከእነዚያ አገራት ጋር በድርድር ላይ መሆኑን አቶ ዝናቡ ቱኑ አስታውቋል፡፡

በክልሉ በተፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እጅ እንዳለበትና በተለይ የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ ዜጎች ላይ ግድያ፣ መፈናቀልና ዝርፊያ መፈጸሙን እንዲሁም በመንግስት ተቋማት ላይም ቃጠሎና ዝርፊያ መፈጸሙን ኃላፊው  በመግለጫው ጠቁመዋል፡፡