የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የመለያ ደንብ ልብስ የቀለምና የዲዛይን ለውጥ ሊደረግበት ነው

የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የመለያ ደንብ ልብስ የቀለምና የዲዛይን ለውጥ ሊደረግበት መሆኑን የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሜጀር ጀኔራል አብዱራህማን እስማኤል ገለጹ።

የደንብ ልብሱን የቀለምና የዲዛይን ለውጥ ማድረግ የመከላከያ ሰራዊቱን የመለያ ደንብ ልብስ በመልበስ በሰራዊቱ ስም ወንጀል የሚፈፅሙ አካላትን ለመቆጣጠር ያስችላልም ተብሏል።

የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሜጀር ጀነራል አብዱራህማን እስማኤል እንደገለጹት የመከላከያ ሰራዊቱን የመለያ ደንብ ልብስ ጥራትና ደረጃውን በጠበቀ የቀለምና ዲዛይን ለውጥ ሊደረግበት ነው።

ፋውንዴሽኑ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 179/2002 በተሰጠው ስልጣን መሰረት ለሰራዊቱ አልባሳትና ሌሎች ወታደራዊ ግብዓቶችን በማምረት አሊያም ገዝቶ ያቀርባል ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚወዱት፣ በጥራት፣ በቀለምና በዲዛይን የተሻለ የመለያ ልብስ እንዲሆን ከተለያዩ አገሮች ተሞክሮ መወሰዱን ገልጸዋል።

የመከላከያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ሃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል ተሾመ ገመቹ በበኩላቸው የመከላከያ ሰራዊቱን አልባሳት መልበስ የሚችለው የሰራዊቱ አባል ብቻ ቢሆንም ተገቢ ቁጥጥር ባለመደረጉ የማይመለከታቸው ግለሰቦች ለብሰውት ተስተውሏል።

አዳዲስ አልባሳት በሚቀርቡበት ወቅት አሮጌዎቹ በአግባቡ ሳይወገዱ በመቅረታቸው ልብሱ በማይመለከታቸው አካላት እጅ ገብቶ የሰራዊቱን ስምና ክብር የሚያጎድፉ የተለያዩ ወንጀሎች እየተፈጸሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣይ በሰራዊቱ አልባሳት ላይ የሚደረገው የቀለም ለውጥ እንዲሁም አዲስ አልባሳት ሲሰጥ ችግሩን ለመፍታት የሚያስቸሉ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ነው ያመለከቱት።

የመከላከያ ሰራዊቱን የመለያ ደንብ ልብስ በመልበስ ወንጀል የሚፈጽሙ አካላት ካሉ በወንጀል እንደሚጠየቁ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡም የመከላከያ ሰራዊቱን የመለያ ደንብ ልብስ መልበስ የሚችለው ሰራዊቱ ብቻ መሆኑን ተረድቶ የማይገባውን ልብስ ባለመልበስ ወንጀል እንዳይፈጸም ሊተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል። (ኢዜአ)