የትግራይ ክልል ምክር ቤት በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀውን የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ተቃወመ

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀውን የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በመቃወም ውሳኔ አስተላለፈ።

ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው በመቐለ ከተማ እያካሄደ ባለው 5ኛ ዓመት 14 መደበኛ ጉባዔው ነው።

ምክር ቤቱ በውሳኔ ሀሳቡ አዋጁ የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የክልላዊ አስተዳደር መብትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንን እንዲጋፋ የሚያደርግ ነው ብሏል።

በተጨማሪም በክልሎች፣ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል መጠራጠር እንዲፈጠር የሚያደርግ እንደሆነም ነው ምክር ቤቱ በውሳኔ ሀሳቡ የገለፀው።

ለዚህም ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሕገ መንግስት የተሰጣቸውን ስልጣን ተክቶ የወሰንና የማንነት ጉዳዮችን ለመመልከት መቋቋሙ ስሕተት ነው ሲል በውሳኔ ሀሳቡ አስፍሯል።

ምክር ቤቱ በመጨረሻም አዋጁን በመቃወም የተዘጋጀውን የውሳኔ ሀሳብ አፅድቋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)