የአስተዳደርና የወሰን ጉዳዮች እልባት ሳይሰጣቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ መተላለፋቸው ተገቢ አይደለም- የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት

በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደርና የወሰን ጉዳዮች እልባት ሳይሰጣቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ ለባለ ዕድለኞች መተላለፋቸው ተገቢ አለመሆኑን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገለፀ።

የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ባወጣው መግለጫ የኦሮሚያ ክልል ጥያቄ እያነሳባቸው ባሉና የክልሉን ወሰን አልፈው የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ ሂደት እንዳይተገበርም አቋም መያዙን ነው የገለፀው።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት በሁሉም አቅጣጫ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ደረጃ በደረጃ እየሰራ መሆኑን በመግለጫው አንስቷል።

በዚህም ትላልቅ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ነው መግለጫው የጠቆመው።

የአዲስ አበባ ጉዳይም ይሁን ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች በሙሉ በቅደም ተከተላቸው መልስ እንዲያገኙ በተሃድሶ ከስምምነት ላይ የተደረሰበት መሆኑን በማንሳትም ይህም እየተሰራበት መሆኑ ተገልጿል።

በመሆኑም ይህ ውሳኔ ስራ ላይ እንዳይውል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጠንካራ አቋም መያዙን በመግለፅ፥ ይህ አቋም በቀዳሚነት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ የመነጨ እንጂ የሀገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች አብሮ የመኖር እሴት ከመጥላት የመነጨ አለመሆኑ ከግንዛቤ ሊገባ ይገባልም ብሏል።

የክልሉ መንግስት ከአዲስ አበባ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ማንኛውንም አጀንዳዎችን እና ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እንደሚመለከተውም ነው በመግለጫው ያስታወቀው።

በአዲስ አበባን እና በዙሪያዋ ተያይዘው የሚከናወኑ ስራዎች ከክልሉ መንግስትና ህዝብ እውቅና ውጪ ለመስራት መታቀዳቸው ህጋዊ ነው ብሎ እንደማያምንም አስታውቋል።

“ትናንት ከህዝብ ጋር የታገልነው የህዝቡን ችግሮች ለመቅረፍ እና ህዝቡን ወደ ተሻለ ብልፅግና ለማሸጋገር ነው ያለው መግለጫው፥ ዛሬም ቢሆን ትናንት ለህዝቡ ቃል የገባናቸውን ድሎች እያስመዘገብን መተናል፤ ይህንንም በማስቀጠል ማንኛውንም የህዝብ ጥያቄ በትግል ለማስመለስ አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን” ብሏል የክልሉ መንግስት።

የኦሮሞ እና የኦሮሚያ መብትና ጥቅምን በማስከበር ወደተሻለ ብልፅግና ለማሸጋገር በህጋዊ መንገድ እንሰራለንም ነው ያለው።

በአዲስ አበባ ጉዳይም ከወሰንና ቤቶች ጉዳይ በዘለለ የከተማዋን የኦሮሞ ባለቤትነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል የክልሉ መንግስት በመግለጫው።