ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ 10 ተከሳሾች የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ በ14 ተከሳሾች ላይ አቃቤ ሕግ የተሻሻለ ክስ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

ተከሳሾች አቃቤ ሕግ ባቀረበው የተሻሻለ ክስ አስተያየት የለንም በማለታቸው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

በእምነት ክህደት ቃላቸው ወንጀሉን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አይደለንም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

1ኛ ተከሳሽ ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው በ3 የተለያዩ ክሶች፣ 2ኛ ተከሳሽ ኮሎኔል በርሄ ወልደሚካኤል በ2 የተለያዩ ክሶች እንዲሁም ከ3ኛ እስከ 14ኛ ያሉ ተከሳሾች በአንድ የክስ አይነት ተከሰው የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡

በተሻሻለው ክስ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያሉ ተከሳሾች በመንግስትና በህዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው በሕግ ከተሰጣቸው ስልጣን ባለፈ ከብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን አሰራር ውጭ ለመርከቦች ጥገና አስተዳደር የ544,702,623 ብር ጉዳት አድርሰዋል፡፡

ከ6ኛ እስከ 14ኛ የተጠቀሱ ተከሳሾች ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር የተለየ ቅርበት በመፍጠር የኮርፖሬሽኑን ወኪል በማደራጀትና ዱባይ በማስቀመጥ፣ ከፍተኛ ወጭ በማውጣት፣ ያለምንም ጨረታና ውድድር የግዥ መመሪያውን በመጣስ፣ ውል በመያዝና ለደላሎች ጭምር በመክፈል የ544,702,623 ብር ጉዳት በማድረስ መከሰሳቸውን ክሱ አስረድቷል፡፡

የተሻሻለው የዐቃቤ ሕግ በ3ኛ ክስ 1ኛ ተከሳሽ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ብቻ የሚመለከት ሲሆን ተከሳሹ የማይገባውን ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት በማሰብ ስልጣኑን በመጠቀም በዓለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ መርከቦቹ መሸጥ አለባቸው የሚለውን የኮሚቴዎች ውሳኔ በማቋረጥ ለኤፔክስ ሺንግ ለተባለ ድርጅት እንዲሸጥ በማዘዙ መርከቦቹ ከተገዙበት 607,432.00 የአሜሪካን ዶላር አንሶ እንዲሸጥ በማድረግ ወንጀል መከሰሳቸውን ያስረዳል፡፡

የተሻሻለው ክስ ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኜው በሁለት ክሶች 2ኛ ተከሳሽ በአንድ ክስ እንዲከሰሱ በማድረግ ተሻሽሏል፡፡

ተከሳሾች ዐቃቤ ሕግ በዛሬው ዕለት ባቀረበው የተሻሻለ ክስ አስተያየት የለንም በማለታቸው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡

ተከሳሾች በእምነት ክህደት ቃላቸው ወንጀሉን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አይደለንም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾች ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ክደው በመከራከራቸው እንደ ክሱ አቀራረብ በክሱ ላይ የተጠቀሱት የሰው ማስረጃዎች እንዲሰሙና እና ማስረጃዎቹም እንዲመረመሩ በማለት ጠይቋል፡፡

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ የወንጀል ችሎት የዐቃቤ ሕግን የሰው ምስክሮች ለመስማትና ማስረጃዎችን ለመመርመር ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 7 ቀን 2011 ቀጠሮ መያዙ ታውቋል፡፡

በችሎቱ ያልቀረቡ 2ኛ ተከሳሽ ኮሎኔል በርሄ ወልደሚካኤል፣ 7ኛ ተከሳሽ ኮሎኔል መሀመድ ብርሃን፣ 13ኛ ተከሳሽ ሚስተር ዋሀድ ራፍ እንዲሁም 14ኛ ተከሳሽ ኡስማን አብዱ እስካሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ባለመዋላቸው በጋዜጣ ጥሪ የተላለፈላቸው መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

(ምንጭ፡- የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ)