የለውጥ ሃይሉ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ማስከበር አልቻልም – ፖለቲከኞች

የለውጥ ሃይሉ  በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን  ማስከበር  አልቻልም ሲሉ ዋልታ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች ገለጹ፡፡

ጋዜጠኛ እና ደራሲ ጥበቡ በለጠ የዶ/ር አብይ አስተዳደር በርካታ ለውጦችን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ መተግበር ቢችልም የህግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ  ተግዳሮቶች አሉበት ብለዋል፡፡

ሰዎችን ዘቅዝቀው የሰቀሉ ወንጀለኞች ለፍርድ ይቀርባሉ ብዬ እጠብቅ ነበር፤ ባንክ ላይ  የተደራጀ ዝርፊያ ሲፈፅሙ፣ ስርአት አልበኝነት ሲነግስ፣ ህግ ሊከበር ሲገባው በዝምታ መታለፉ ተገቢ እንዳልነበር አቶ ጥበቡ  አስታውሰዋል፡፡

ፖለቲከኛው  አቶ ግርማ ሰይፉ  ደግሞ  ለውጡ ከላይኛው አካል እንጂ የታችኛው መዋቅር ድረስ አለመውረዱ ለህግ የበላይነት አለመከበር ምክንያት ነው ብሏል፡፡

ፖሊስን ጨምሮ የደህንነት መዋቅሩን በለውጡ ቅኝት አሰልጥኖ ለማሰማራት የለውጡ እድሜ አጭር መሆንም ሌላኛው ችግር ነው እንደ አቶ ግርማ ገለፃ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳንይስ መምህሩ  ዶ/ር መረራ ጉዲና  በበኩላቸው ችግሩ ከለውጡ በፊት የነበረው የታችኛው አመራር አሁንም በለውጥ መንፈስ ካለመቃኘቱ የሚመነጭ ነው ብለዋል፡፡

መንግስትን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን ስራ አለማከወናቸው የህግ የበላይነት  እንዳይከበር  አበርክቶው የጎላ ነበርም ብለዋል፡፡

ወርልድ ጀስቲስ ፕሮጀክት በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት የህግ የበላይነት ካልተከበረባቸው 126 ሃገራት ኢትዮጵያ 118ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡