ኢህአዴግ ሀገራዊ ለዉጡን ለማስቀጠል የጋራ የአስተሳሰብ አቋም ሊያመጣ እንደሚገባው ተገለጸ

ባለፈዉ አንድ ዓመት የተጀመረዉን ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ለዉጥ ለማስቀጠል ኢህአዴግ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ የጋራ አቋም ሊይዝና እርስ በእርስ በመደማመጥ ወደ ሀሳብ አንድነት መምጣት እንደሚገባዉ ተገለጸ።  

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ምሁር የሆኑት ዶክተር ኬይረዲን ተዘራ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የሀሳብ ልዩነት ካላቸዉ ከዚህ በፊት በለመዱት የዉይይት ልምድ ችግሮቻቸዉን በጠረጴዛ ዙሪያ መክረዉ ወደ ጋራ የፖለቲካ አቋም መምጣት ይገባቸዋል ብለዋል።

የድርጅቱ ስምምነትና አንድነት የሕዝቡን ስነልቦና የሚገነባ ከመሆኑም ባለፈ ዜጎች በሀገራቸዉ ቀጣይ እጣ ፋንታ ላይ ተስፈኞች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ሲሉም አክለዋል።

እንደ ዶክተር ኬይረዲን ማብራሪያ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ተቻችሎና በጋራ የመኖር ጠንካራ እሴት ያላቸዉ ሕዝቦች በመሆናቸዉ ሀገሪቱ እንደነ ዩጎዝላቪያ የመበታተን አደጋ ተጋርጦባታል የሚለዉ የአንዳንዶች አስተያየት ከስጋት የዘለለ አይደለም፡፡ 

የህዝቡ ጠንካራ የሀገር ፍቅርና እርስ በራሱ ያለዉ ጠንካራ የአንድነትና የአብሮነት መስተጋብር ለዚህ ዋስትና ይሆናል ብለዋል።

ዜጎች በመንግስት ተስፋን እንዳያጡና ለዉጡም እንዳይቀለበስ መንግስት የህግ የበላይነትን ሊያስከብር እንደሚገባ የገለፁት ዶክተር ኬይረዲን በዚህ ሂደት ዉስጥ ደግሞ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች የበኩላቸዉን መወጣት ይገባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።