በኤርትራ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የነበረው የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ወደ ሀገሩ ገባ

መቀመጫውን ኤርትራ በማድርግ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የቆየው የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) ወደ ሀገሩ ገብቷል።

የንቅናቄው አባላትና አመራሮች ጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ደጋፊዎቻቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ በሀገር ውስጥ የተፈጠረውን ሰላም በመጠቀም ሰላማዊ ትግል ለመጀመር በመወሰን ወደ ሀገር መግባቱን የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ኡኬሎ ኡኪዲ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ንቅናቄው የትጥቅ ትግልን አማራጭ በማድረግ ሲንቀሳቀስ መቆየቱንም አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ንቅናቄው በቅርቡ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በኤርትራ ሲያካሂድ የነበረውን የትጥቅ ትግል አቁሞ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በመወሰን ከኤርትራ ወደ ጋምቤላ ገብቷል ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ህዝቦች እንደሌሎቹ የህዝብ ድርጅቶች ጠንካራ ድርጅት ባለመኖሩ ባለፉት ዓመታት ህዝቡ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን አስታውሰዋል።

የንቅናቄው አመራርና አባላት ወደ ጋምቤላ ሲገቡ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላደረጉላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በአቀባበል ስነ-ስረዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው፥ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ የትጥቅ ትግሉን በመተው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መወሰኑ የሚበረታታ እንደሆነ ገልፀዋል።

የክልሉ መሪ ድርጅት ጋህአዴንም ሆነ ጋህነን እና ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሃሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳን ልዩነታቸውን በማጥበብ ለክልሉ ሁለንተናዊ ልማት መስራት ይገባል ነው ያሉት።

ለዚህም የክልሉ መሪ ድርጅትና መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ወደ ክልሉ ለገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች በጋራ ለመስራትና ለውጡን ለማስቀጠል ዝግጁ እንደሆነ ማስታወቃቸውን ተገልጿል፡፡

(ምንጭ፡- ኤፍቢሲ)