የአማራ ክልል ሕዝቦች ትግል ወሳኝ ምዕራፍን የተቆናጠጠ መሆኑን ተገለጸ

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ የአማራን ሕዝብ ትግል ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ለመምራት በተደረገው እንቅስቃሴ የሕዝብ አጀንዳዎች መንግስታዊ ባለቤት አግኝተው ከሕዝቡ ጋር በእጅጉ የመቀራረብ ዕድል ከመፈጠሩም በላይ ለጥያቄዎችም ዘላቂ መፍትሄ ለመሻት ጠንካራ መደላድሎች ተፈጥረዋል ብሏል፡፡

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን በማጠናከር የአማራን ሕዝብ መሰረታዊ አጀንዳዎች መሬት ለማስያዝ በአንድነት መረባረብ ይገባል ያለው መግለጫው የአማራ ክልል ሕዝቦች ትግል ወሳኝ ምዕራፍን መቆናጠጡንም አትቷል፡፡

የአማራን ሕዝብ ትግል ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ለመምራት በተደረገው እንቅስቃሴ የሕዝብ አጀንዳዎች መንግስታዊ ባለቤት ማግኘታቸውን መግለጫው ያስረዳል፡፡

የአማራ ሕዝብ ትግል ፈር እየያዘ ውጤቶችን ማስመዘገበ የቻለው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ቋጠሮ በመለየት ሂደት ከለውጥ ሃይሎች ጋር በተደረገው መናበብ የቋጠሮውን ዋና አካባቢ መጨበጥ በመቻሉ ነው ብሏል፡፡

በሀገር ግንባታ ሂደት በሕዝቦች መካከል መከፋፈልና መጠራጠር እንዲሰፋ እና እይታን የሚጋርዱ የፈጠራ ግድግዳዎች እንዲበረቱ የተሰራው ሴራ ለማክሸፍ  የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን ትስስር እና ግንኙነትን ማጠናከር ችግሩን ለመፍታት አንደኛው መፍትሄ ተደርጎ ሊወሰድ እደሚገባም መግለጫው ያትታል፡፡

በዚህ ሳምንትም በአምቦ ከተማ የተካሄደው የአማራና የኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የተሰራው ስራና የታየው አዎንታዊ ምላሽ ትልቅ ፖለቲካዊና ሕዝባዊ ድል መሆኑንም መግለጫው ጠቅሷል፡፡ ይህን መሰል ግንኙነት ከሌሎች ሕዝቦች ጋርም እየሰፋና እየተጠናከረ መሄድ እዳለባቸው መግለጫው አትቷል፡፡

የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት ድል ኢትዮጵያን ለመታደግ እና የሕዝብ ጥያቄዎችን ምላሽ እየሰጡ ወደፊት መራመድ እንደሆነ መግባባት መቻሉ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ግንኙነቱን አስመልክቶ አዎንታዊም አሉታዊም በሆነ መልኩ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ መድረክ ውስጥ የተለያዩ ስሜቶች መስተዋላቸውንም መግለጫው ጠቅሷል፡፡

በመጀመሪያ ሁሉም ሰው ልብ ማለት የሚገባው ጉዳይ የአማራን እና የኦሮሞን ሕዝብ በማለያየት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚፈልጉ አካላት ግንኙነትን ለማጠልሸት መሞከራቸው የኖረ፤ ያለና የሚኖር ተግባር መሆኑ ነው ያለው መግለጫው የሃይሉ አሰላለፉ ግልፅ ነው  ብሏል፡፡

በዚህ ሃይል አሰላለፍ ላይ ቀጣይነት ያለው የጋራ ትግል የሚጠይቅ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው የእነዚህ ሃይሎች ዕውነተኛ አጀንዳ በማህበራዊ ሚዲያ የማያቋርጥ ዘመቻ በማካሄድ የህዝቦቹን እውነተኛ አጀንዳ ማሳት የሚቻል መስሏቸው የሚደክሙ መሆናቸው መታወቅ አለበት ብሏል፡፡

ሁለተኛው አሰላለፍ ደግሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በከፊል የሚቀበል መስሎ ነገር ግን በይዘት ደረጃ የተወሰኑ ጉዳዮችን በመምዘዝ ከትልቁ ስዕል እየወጡ ሆን ብለውም ሆነ ሳይረዱት ከዚህ በላይ ለጠቀስናቸው የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ዱላ ማቀበል ላይ የሚታትሩ መኖራቸውን መግለጫው ጠቅሷል፡፡

በአምቦ በተካሄደው የአማራና የኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሠ-መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን የአዲስ አበባን ጉዳይ አስመልክቶ ከተሳታፊ ለተነሳላቸው ጥያቄ ከሰጡት ምላሽ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሃሳቦች እየተንሸራሸሩ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ማከል ጠቃሚ መሆኑንም መግለጫው አትቷል፡፡

የአዲስ አበባ ጉዳይ የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት የሚራመድበት አንድ አጀንዳ መሆኑን መግለጫው ጠቅሶ የአዲስ አበባ ጉዳይ ከባለቤትነት ጋር በተያያዘ እና ከህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች ጋር እየተጣመረ የሚቀርብ አጀንዳ መሆኑንም ገልጿል፡፡ በሁለቱም ጉዳዮች ላይ የክልሉ መንግስት የያዘው አቋም ግልፅ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን ባለቤትነት በተመለከተ ባለቤቶች ነዋሪዎቿና ሁሉም ከተማዋን የገነቡ ኢትዮጵያዊያን ናቸው የሚል ግልፅ አቋም አዴፓ ማራመዱን መግለጫው ገልጾ በዚህ ጉዳይ ላይ ዛሬም የተለወጠ አቋም እንደሌለ አስገዝቧል፡፡

መግለጫው ህገ-መንግስቱን በሚመለከት፤ መሻሻል በሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ህገ-መንግስቱን መፈተሽ፤ ማሻሻል እና ማስተካከል የሚገባ መሆኑን ጠቅሶ መሻሻል የሚገባቸው ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች ሕዝቡን ባሳተፈ እና በዴሞክራሲያዊ አግባብ እስኪሻሻል ድረስ የሚመራበት ሰነድ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የአማራን ሕዝብ ጥቅም በዘላቂነት ለማስጠበቅ እደሚታገል የገለጸው የክልሉ መንግስት ጠንካራ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የማይተካ ሚናው እንደሚጫወት መግለጫው አትቷል፡፡ በዚህ ሂደት የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎች እና አክቲቪስቶች ጋር ተናቦ እና ተጋግዞ መስራት የአማራን ሕዝብ ፖለቲካ ወደፊት እንደሚያራምደው መግለጫው አትቷል፡፡

በዚህ ወቅት የአማራ ሕዝብ አጀንዳዎችን ሊያስጥሉን ያሰፈሰፉ ዕኩይ ሃይሎች ብዙ መሆናቸውን የጠቆመው መግለጫው የአማራ ሕዝብ በመደራጀት እና በአዲስ የትግል ምዕራፍ ውስጥ ሆኖም በየአካባቢው የተለያዩ ጥቃቶች ሰለባ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የክልሉ መንግስት በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች አካባቢዎች የማንነት ጥያቄን ሽፋን በማድረግ የገጠመውን አስከፊ ጥፋት ከሰሞኑ ደግሞ በምስራቁ የአማራ ክልል ተመሳሳይ መልክ ተላብሶ መፈፅሙን መግለጫው አውስቷል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት መጠነ-ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ የሚንገኝ መሆኑን የተቀሰው መግለጫው ችግሮቹን ቀስ በቀስ በመፈታት ላይ ናቸው ብሏል፡፡

በመሆኑም የአማራ ክልላዊ መንግስት የአማራ ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ለማረጋገጥ እና ይህን ወቅት በአሸናፊነት ለመሻገር እርስ በእርስ ተጠላልፎ ከመውደቅ አጉል በሽታ በመውጣት በጋራ ለሕዝቡ አጀንዳዎች መሬት መንካት ዴሞክራሲያዊ ትግል፤ ትብብር እና አብሮነት እዲዳብር ለመላው ባለድርሻ አካላት ጥሪ በማቅረብ መግለጫውን ቋጭቷል፡፡