አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ቃለመሃላ ፈፀሙ

የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው ዛሬ ቃላመሃላ ፈፅመዋል።
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው 34ኛ መደበኛ ስብሰባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ የ3 ሚኒስትሮችን ሹመት በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁ ይታወሳል።  

ይሁን እንጂ በዕለቱ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምክር ቤቱ ቀርበው ቃለመሃላ አለመፈጸማቸው ይታወቃል።

በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ አንቀጽ 111 መሰረት ዛሬ ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም በምክር ቤቱ አፈጉባኤ ፊት ቀርበው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ አማካኝነት የተጣለባቸውን የህዝብና የመንግስት ሃላፊነት በቅንነት፣ በታታሪነት፣ ህግና ደንብን መሰረት በማድረግ ለመወጣት ቃለመሃላ ፈፅመዋል።

የምክር ቤቱ አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ለተሿሚ ሚኒስትሩ ስኬታማ የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልፀውላቸዋል፡፡

(ምንጭ ፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት)