የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር የቤልት ኤንድ ሮድ ተነሳሽነት ሀገራትን የማገናኘት መርህ ማሳያ ነው – ጠ/ሚ አብይ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቻይና በሁለተኛው የቤልት ኤንድ ሮድ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ጉባኤ መክፈቻ ላይ እየተካፈሉ ነው።

በጉባኤው ላይ በዚህ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ውስጥ የሚገኙ ሀገራት መሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ

በመክፈቻው ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ያሳለጠ የቤልት ኤንድ ሮድ ተነሳሽነት ሀገራትን የማገናኘት መርህም ማሳያ የሆነ  ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን ኢንቨስትመንት መር የኢኮኖሚ ፖሊሲና የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማስረዳትም ኢንቨስተሮች አዲስ በተከፈቱ  ዘርፎች ላይመዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ አበረታተዋል።

በዚህ ማእቀፍ ውስጥ  ቻይና ለኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የንግድ አጋር ስትሆን ዋነኛ የቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ምንጭም ናት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚህ የቻይና ጉብኝታቸው ወቅትም ሁለቱ ሀገራ ለቤልት ኤንድ ሮድ ማዕቀፍ የአምስት አመት ትብብር እቅድ እና የቻይና አፍሪካ የትብብር መድረክ (FOCAC) ስር የሚካሄድ ትብብር መተግበሪያ መግባቢያ ሰነድ ላይ መፈራረማቸው ከጠቅላይ ሚኒስር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በፈረንጆቹ 2013 በቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አማካኝነት መተግበር የጀመረ ሲሆን፥ በ2017 የመጀመሪያ ፎረሙን አካሂዷል።

ኢኒሼቲቩ አፍሪካን ጨምሮ፣ ደቡብ ምስራቅ እስያን እና የአውሮፓ ሃገራትን ያካተተና ሃገራትን በመንገድና በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር አላማን ያነገበ መሆኑ ይነገራል።

ከ65 በላይ ሃገራትን ያቀፈው ይህ ኢኒሼቲቭ ለቀጠናዊ ትስስር ቅድሚያ በመስጠት የሚሰራም ነው።
የፖሊሲ፣ መሰረተ ልማት፣ ንግድ ፋይናንስ እና የህዝብ ለህዝብ ትብብርን መሰረት ያደረገ የትብብር ማዕቀፍም ነው።