በዳንጉር ወረዳ የተከሰተውን ግጭት የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ወደ አካባቢው መግባቱ ተገለጸ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዳንጉር ወረዳ የተከሰተውን ግጭት የሚያጣራ የተደራጀ የምርመራ ቡድን ወደ አካባቢው መግባቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሀሰን ትላንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ግጭት የተከሰተበት የዳንጉር ወረዳ ማምቡክ ከተማና አካባቢው በፌዴራልና ክልል የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡

ግጭቱ የተከሰተበት አካባቢ እየተረጋጋ መሆኑንም አመልክተው ትላንት ረፋድ ላይ የተደራጀ የክልሉ የምርመራ ቡድን ወደ አካባቢው ገብቷል ብለዋል።

በሌሎች አንዳንድ የወረዳው ቀበሌዎች ትላንት ረፋድ ላይ ተመሳሳይ ግጭት መከሰቱን ጠቁመው በዚህም ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን እና የወደመውን ንብረት ትክክለኛ መጠን ለመግለጽ እንደሚቸገሩ አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል በአካባቢው የተከሰተውን ችግር በጋራ ለመፍታት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰማኸኝ አስረስ የሁለቱ ክልል መንግስታት ዜጎችን ከጉዳት ለመጠበቅና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

(ምንጭ፡- ኢዜአ)