ዓለም አቀፉ የፕሬስ ነፃነት ቀን ዛሬም ቀጥሏል

በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ከትላንት ጀምሮ እየተካሄደ ያለው ዓለም አቀፉ የፕሬስ ነፃነት ቀን ዛሬም በአፍሪካ ህብረት እየተካሄደ ይገኛል።

በዛሬው የሁለተኛው ቀን ውሎ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማህማት እንዲሁም የዩኒስኮ ጄነራል ዳይሬርተር ዶክተር ቬየራ ሶንጊያ የመክፈቻ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

"ሚዲያ በዴሞክራሲ ጋዜጠኝነትና ምርጫ በዘመነ መረጃ ብክለት" በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ የመገናኛ ብዙሃን ሚና በተለይ በቀውስ ወቅት እና በሃገራዊ ምርጫ ወቅት ሃላፊነታቸው ምን ሊሆን ይገባል? በሚል ውይይት ይደረጋል። የአፍሪካ ህብረት የጋዜጠኞችን ደህንነት በተመለከተ ያወጣቸው ደንቦች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት እንደሚደረግባቸውም ይጠበቃል።
የመንግስታቱ ድርጅት የፕሬስና የመናገር ነጻነትን ዕውን ለማድረግ ሚድያዎች ሊያቆጠቁጡ የሚችሉበት ምቹ ህጋዊ ማዕቀፍ መኖር፣ ህጎችን ተግባራዊ የሚያደርግ የፖለቲካ ምህዳር፣ የሰፊውን ህዝብ ጥቅም መሰረት ያደረጉ መረጃዎች ከሚመለከተው አካል በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ መኖሩ እና ሚድያዎች የሚያሰራጯዋቸውን መረጃዎች የሚጠቀሙ አካላት ያላቸው ግንዛቤ እና በዕውቀት ላይ ተመስርቶ ሚድያዎችን የመተቸት ብቃት ማደግ እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡

ኢትዮጵያ በፕሬስ ነጻነት ረገድ በፈረንጆቹ አቆጣጠር አምና ከነበረችበት በአለም 150ኛ ደረጃ በ2019 ወደ 110 በመውረድ 40 ደረጃዎችን ማሻሻሏን "ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ" በቅርቡ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

መረጃን በነፃነት የማግኘትና የመስጠት መብት የተገደበ በመሆኑ እና መንግስት የመገናኛ ብዙኃን በሚያስገቧቸው እቃዎች ላይ የሚጥለው ታክስ ከፍተኛ መሆን በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ላይ የተጋረጡ ፈተናዎች ናቸው ተብሏል፡፡

የፕሬስ ነጻነት ቀን የመረጃ ነጻነትን መሰረታዊ መርሆዎችን ለመዘከር እንዲሁም ለፕሬስ ነጻነት ሲሉ ውድ ህይወታቸውን ያጡና ጉዳት የደረሰባቸውን ጋዜጠኞች ለመዘከር በአለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡