67ኛው የኢጋድ የሚኒሰትሮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ተጠናቀቀ

በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የተካሄደው 67ኛው የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የወቅቱ የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ገዱ አንዳርጋችው የስብሰባውን ውጤት በተመለከተ ዛሬ ለደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ገለጻ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ በገለጻቸው የደቡብ ሱዳን ተደራዳሪ ወገኖች ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት የቅድመ ሽግግር ጊዜው ለተጨማሪ 6 ወራት እንዲራዘም የደረሱትን ስምምነት የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሙሉ በሙሉ መቀበሉን ገልጸዋል።

በተደራዳሪ ወገኖች በኩል የተደረሱ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ 100 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ በመንግስት በኩል መመደቡን ምክር ቤቱ በአድናቆት እንደተመለከተውና ለዚህም በምክር ቤቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ዓለም አቀፍ አካላት ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያነሳሳቸውም ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።