2ኛው የአዲስ ወግ የባለሙያዎች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

ሁለተኛው የአዲስ ወግ የባለሙያዎች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

የውይይት መድረኩ የሕግ የበላይነት በዴሞክራሲ የሽግግር ሂደት ወቅት በሚል ርዕስ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ በሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ በዶክተር ዳኛቸው አሰፋና በዶክተር ጌታቸው አሰፋ አቅራቢነት እየተካሄደ ነው፡፡

የመነሻ ሃሳብ ካቀረቡት መካከል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ዓለም አቀፍ ሪፖርትን በማጣቀስ  ኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ ያስመዘገበችውን እመርታ አንሥተዋል፡፡

ይህ የሽግግር ወቅት መንግሥት ሕግን ለራሱ ጥቅም ከማዋል ይልቅ የሕግ የበላይነትን ወደ ተቋማዊነት ማሸጋገር እንደሚያስፈልግም ወ/ሮ መዓዛ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶክተር ጌታቸው አሰፋ በበኩላቸው በሕግ መግዛትና በሕግ መምራት መካከል ያለውን ልዩነት ለመገንዘብ ከየት መጣን? የትስ ነን? የሚለውን መረዳት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በበኩላቸው የሕግ የበላይነትን ፍልስፍና መሠረቶች፣ በለውጡ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ የተገኙ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ዙሪያ አቅርበዋል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ባቀረቡት ጽሑፋቸው ዜጎችን ያሳተፈ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የመንግሥትን ቁርጠኝነት በመግለጽ የተቋማት ሥነ ልቡናዊ አወቃቀር ፀረ ዴሞክራሲያዊነት እንደሚያዘነብልና ይኽንን መቀየር ትልቅ ሥራና ጊዜ እንደሚፈልግ አንሥተዋል።

(ምንጭ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት)