በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱ ህዝባዊ ኮንፈረንሶች ስኬታማ እንደነበሩ ተገለጸ

ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በሁሉም ዞኖች የተካሄዱ ህዝባዊ ኮንፈረንሶች ስኬታማና ግባቸውን የመቱ እንደነበሩ ተገለጸ፡፡

ይህንኑን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃኑ መግለጫ የሰጡት የኦዲፒ ማዕከላዊ ጽ/ቤት የህዝብ አስተያየትና ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ መንግስት ህብረተሰቡን በብሔርና ሃይማኖት ለማጋጫት የሚንቀሳቀሱ አካላትን አይታገስም ነው ያሉት፡፡

አንድ ነን በሚል መሪ ሃሳብ ላይ በማጠንጠን፣ የህብረተሰቡንም ወንድማማችነት ለማስረዳት ከሰኞ ጀምሮ በመላው የኦሮሚያ ክልል ከዞን እስከ ቀበሌ ሲካሄድ በነበረው የህዝቦች አንድነት የጋራ መድረክ ለፖለቲካ ጥቅም ብቻ የሚደረገው ህዝብን የመከፋፈል ሩጫ ተወግዟል፡፡

በክልሉ የሚኖሩ የተለያዩ ህዝቦች ተሳታፊ በነበሩበት በዚህ መድረክም ዘመናትን ተሻግሮ በመጋመድ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰውን የህዝቦች አንድነትና ትስስር ማፍረስ የሚቻለው አለመኖሩም ተወስቷል፡፡

ከውስን የክልሉ ቆላማ ቀበሌዎች በስተቀር በክልሉ ሁሉም 20 ዞኖች ኮንፈረንሱ መጠናቀቁን ተከትሉ፤ የመድረኩን ውጤታማነት በማስመልከት መግለጫ የሰጠው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዲፒ በወንድማማችነት የምክክር መድረኩ በክልሉ የሚኖሩ ሁሉም ብሔሮች ተሳታፊ እንደነበሩ በማስገንዘብ ውጤታማነቱንም አብስረዋል፡፡

በማህበራዊ እና ሌሎችም ሜይን ስትሪም ሚዲያ ህብረተሰቡን ስጋት ውስጥ የሚከቱ አሉባልታዎች ሲነዙ እንደነበርና ይህም በመተባበር አብሮ በኖረው ህዝብ መሃል ስጋትን ፈጥሮ የነበረ በመሆኑ ስጋቱን ማክሸፍ የኮንፈረንሱ ዋነኛ ዓላማ ነበር፡፡

ህዝቦችን በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍን በመሻት ውዥንብር ለሚፈጥሩ ህዝብ ዘንድ በአንድነት ለመኖት አንዳችም ማቅማማት አለመኖሩን ማሳየት ደግሞ ሌላኛው የኮንፈረንሱ ውጥን መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በህዝባዊ ኮንፈረንሱ ከህብረተሰቡ ዘንድ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የመሰረተ ልማቶች ጉዳይ አንዱ ነው፡፡

በዋናነት ግን መንግስት የህዝቦችን ሰላም በማደፍረስ ወዲያ ወዲህ የሚሉትን የህግ የበላይነት በማስከበር ማስቆም አለበት የሚል ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ መንግስት ከመዋቅሩ አመራሮችም ጭምር ህዝብን በማጋጨት የተሳተፉትን በህግ ጥላ ስር እያዋለ እንደሚገኝ አቶ ታዬ አረጋግጠዋል፡፡

ሰሞኑን በአሰላ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ሃይማኖታዊ መልክ ለማልበስ ጥረቶች ተደርገው እንደነበርም በመግለጫው ተገልጿል፡፡

ችግሩን ለመፍጠር በማህበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳዎች አስቀድመውም መጀመራቸውም ተጠቁሟል፡፡

እነዚህ አካላትን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል ምርመራዎች መጀመራቸውና እስካሁንም በቁጥጥር ስር የዋሉ መኖራቸውም ነው የተገለጸው፡፡

በሃላፊነት ከማይሰሩ መገናኛ ብዙሃን ጋር ተያይዞ መንግስት እስካሁን በዴሞክራሲ ጅማሮ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች አድርጎ የተመለከታቸውን የህግ ጥሰቶች የህግ የበላይነትን በማስከበርና አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ለማስተካከል ይገደዳል ሲሉም አቶ ታዬ ደንደአ አስረድተዋል፡፡