የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እጩ አባላትን ሕብረተሰቡ እንዲጠቁም ጥሪ ቀረበ

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እጩ ስራ አመራር ቦርድ መልማይ ኮሚቴ እጩ የቦርድ አባላትን እስከ ግንቦት 22 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ መጠቆም እንደሚቻል አስታወቀ፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለጸው አባላቱን ለመጠቆም የሚያስችሉ መስፈርቶችና የጥቆማ ዘዴዎች መለየታቸው ገልጸው እስከ ሰኔ 10/2011 ዓ.ም ድረስ የመጨረሻ እጩዎችን እንደሚለዩ ጠቁመዋል፡፡

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 5/11 እጩ የስራ አመራር ቦርድ አባላት አባላት መልማይ ማቋቋም እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

በዚህም መሰረት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሰያሚነት እጩ የስራ አመራር ቦርድ መልማይ ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከሚያዚያ 25 ቀን ጀምሮ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ እጩ ጥቆማዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የገለጸው ኮሚቴው መላ ኢትዮጵያዊያን እስከ ግንቦት 22 ድረስ ጥቆማቸውን ማቅረብ እንደሚችሉም አስታውቋል፡፡

ለእጩነት የሚቀርቡ አካላት ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶችን ያመላከተው ኮሚቴው የጥቆማ አቀራረብ ዘዴዎችንም ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህ መሰረት በዜግነት ኢትዮጰያዊና ከማንኛውም የፖለቲካ ተሳትፎ ገለልተኛ የሆኑ፣ የሙያ ብቃታቸው የተመሰከረላቸውና መልካም ስነ ምግባር ያላቸው መሆን አለባቸውም ነው ያሉት። ፈቃደኛነትና ታማኝነት ዋነኛ መስፈርቶች መሆናቸውንም በመግለጫቸው አንስተዋል።

ኮሚቴው ጥቆማዎችን በመቀበል እና አስፈላጊ የማጣራት ስራ በማከናወን እስከ ሰኔ 10/ 2011 ዓም ድረስ የመጨረሻ 20 እጩዎችን ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርብ ዶክተር መሸሻ ገልጸዋል፡፡

ለጥቆማ፡-

ኢ- ሜል nbe2019@gmail.com

ስልክ – 011 515 90 74/ 011 551 93 64

ፋክስ – 011 551 26 43

ፖስታ ሳጥን ቁጥር – 195 አዲስ አበባ

በተጨማሪ በአካል ቀይ መስቀል ራስ ደስታ ዳምጠው መንገድ ጋንዲ ሆስፒታል አጠገብ በማህበሩ ዋና ፀሐፊ ቢሮ በተዘጋጀው ዝግ ሳጥን ውስጥ ምርጫቸውን ማስቀመጥ ይችላሉ።