ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት ወደ ደቡብ አፍሪካ አቀኑ

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት ወደ ደቡብ አፍሪካ አቀኑ፡፡

ደቡብ አፍሪካ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡትን ስድስተኛውን መሪዋን የፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛን በዐለ ሲመት በነገው ዕለት ታከብራለች፡፡

በዚሁ ስነስርዐት ላይ ለመሳተፍ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ዛሬ ከቀትር በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸው ከፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የበዐለ ሲመቱ ስነስርዐት በፕሪቶሪያ በሚገኘው ሎፍተስ ቨርስፊልድ ስታዲየም የሚከናወን ሲሆን፣ የሀገራትና የመንግስታት መሪዎች፣ የአለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች እንዲሁም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት በሀገሪቱ በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ማሸነፉን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ የሀገሪቱ ፓርላማ ሲሪል ራማፎዛን በፕሬዝዳንትነት መሰየሙ ይታወሳል፡፡