የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳጋቸው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ጋር ተወያዩ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ክወሲ ኳርተይ ጋር ተወያዩ፡፡

ምክትል ሊቀ-መንበሩ የአፍሪካ ህብረት ለያዘው መዋቅራዊ ማሻሻያ እያበረከቱት ያለውን ገንቢ የመሪነት ሚና ሚኒስትሩ አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ ለህብረቱ ኮሚሽን እቅዶችና ግቦች መሳካት ያላትን የቆዬ ታሪካዊ ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ጠንካራ፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት የሰፈነበት እንዲሁም በስራው ውጤታማ አፍሪካዊ ተቋም እንዲሆን ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎዋን እንድምትገፋበትም አስታውቀዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀ-መንበር ክወሲ ኳርተይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጀምሮ እስካሁን ላሳየችው የማይናወጥ የአፍሪካዊነት ተጋድሎ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ጋር ባለው መስተጋብር ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ይህም በሁሉም ዘርፎች ተጠናክሮ እንድሚቀጥል ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳጋገጡላቸው ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።