የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች በቤተ-መንግስት ጉብኝት አደረጉ

የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች በዛሬው ዕለት በቤተ-መንግስት ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝታቸው ወቅትም በቤተ-መንግስቱ ውስጥ እየተደረገ ያለውን የኪነ-ህንፃ ዕድሳት እና ግንባታ ተመልክተዋል፡፡ በቤተ-መንግስቱ ውስጥ ያሉ ታሪካዊ አሻራዎችን በተመለከተ እና አዳዲስ ቤተ መንግስቱን ለማስዋብ እንዲሁም ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ባለው ስራም ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡

በተጨማሪም በሀገሪቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ለውጥ ሂደቶች ዙሪያ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገበችው እመርታዊ የኢኮኖሚ ለውጥ እና ባለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ኢኮኖሚው ላይ የደረሰው ጫና እንዲሁም መንግስት ከለውጡ በኋላ የወሰዳቸው የምጣኔ ሀብት ሪፎርሞችን በተመለከተ ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡

የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡም የተደረገላቸውን ገለፃ መሠረት በማድረግ ሀሳብና አስተያየቶችን አንስተው ተጨማሪ ማብራሪያ በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በመጨረሻም ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ በቤተ-መንግስት የችግኝ ተከላን ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር አካሂደዋል፡፡