ኢትዮጵያ በሱዳን ያለውን ቀውስ ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት አሜሪካ እንደምታደንቅ አስታወቀች

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናዥ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅት በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ነው የተነገረው፡፡

ቲቦር ናዥ ካርቱም የነበራቸው ቆይታ እና የታዘቡትን ጉዳይ በተመለከተ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሁለቱን ወገኖች ለማቀራረብ እየወዱሰት ያለውን እርምጃ አሜሪካ እንደምታደንቅ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ልዩ መልዕክተኞች የሚያደርጉትን ጥረት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉም ቲቦር ናዥ ተናግረዋል፡፡

ረዳት ሴክሬታሪው አሜሪካ በኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደሯ የነበሩትን አምባሳደር ዶናልድ ቡዝን በሱዳን ጉዳይ ልዩ ልኡክ አድርጋ መሰየሟን በመግለፅ የተቀናጀ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚኒስትር አቶ አገዱ በበኩላቸው የሱዳን ሰላምና መረጋጋትን መደገፍ ማለት በአጠቃላይ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ የሚያሻው መሆኑን እንደገለፁ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡