68ኛው የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ልዩ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀመረ

68ኛው የኢጋድ የሚኒስትሮች ልዩ ጉባኤ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የወቅቱ የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በዛሬው ዕለት በይፋ ተከፍቷል፡፡

አቶ ገዱ በመክፈቻ ንግግራቸው በሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውንና በቀሪ የልዩነት ጉዳዮች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ እና የለውጥ ሀይሎች ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እና ከዚህ በፊት በጀመሩት መሰረት ወደ ውይይት እንዲመጡ የተጀመረውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች ጠብ አጫሪ መግለጫዎችን ከማውጣት እንዲቆጠቡና ውጥረትን ለማርገብ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ እኤአ ሰኔ 7 ቀን 2019 ከሁለቱም ወገኖች ጋር ባደረጉት ወጤታማ ውይይት መሰረት ውጥረቱን ለማርገብና ቀጣይ የድርድር ሂደቱን ለመደገፍ ልዩ መልዕክተኛ መሰየማቸውን አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ ሪፖርት ተሰምቶ ጠቃሚ የሆነ ውይይት ማድረግ እንደሚገባም ሚኒስትሩ በንግግራቸው ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ከደቡብ ሱዳን ጋር በተያያዝ ጁባ በተካሄደው 67ኛው የሚኒስትሮች ስብሰባ በተደረሰው ስምምነት መሰረት አፈፃፀሙን መገምገም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በዛሬው የኢጋድ ልዩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ኢትዮጵያን ጨምሮ የጅቡቲ፣ የኬንያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የኡጋንዳ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መገኘታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡