አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ያልተያዙ ተከሳሾች በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ተሰጠ

አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ባልተያዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከሳሾች በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ ኢንዲደረግላቸው ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

በዚህም መዝገብ 26 ተከሳሾች ያሉ ሲሆን፣ አቃቢ ህግ የሚያቀርበውን የሰው ምስክር ለመስማት ሐምሌ 18፣ 23፣ 24፣ 25 እና 30/2011 ዓ.ም ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ በፊት አቃቢ ህግ ለምስክሮቹ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ያቀረበው ማመልከቻ የምስክሮችን አድራሻ ባለመጥቀሱ አሻሽሎ ኢንዲያቀርብም ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

የጋዜጣ ጥሪ ውጤቱንና ተሻሽሎ የሚቀርበውን የምስክሮች ጥበቃ አቤቱታ ለመጠባበቅ ችሎቱ ለሐምሌ 9/2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል በቀድሞ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል አብዲኑር መሀመድ፣ ኮሚሽነር አብዱላሂ አህመድና ወይዘሮ ዘምዘም ሀሰን ማንነታቸውን የሚያረጋግጥላቸውን ማስረጃ ባቀረቡት መሰረት ሰኔ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሶማሌ ክልል ዘርንና ኃይማኖትን ለይቶ በተፈጸመው ጥቃት ላይ የነበራቸውን ሚና የሚያስረዳ ክስ ተነቦላቸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሻምበል አይድድ በደል በሚል አቃቢ ህግ ክስ የመሰረተባቸው ተከሳሽ ምክትል ኢንስፔክተር አይድድ ራጊ መሆናቸውን የሚያስረዱ ሰነዶች ዛሬ በዋለው ችሎት ያቀረቡት ማስረጃ ተቀባይነት አግንቷል፡፡

ተከሳሹን በተመለከተ አቃቢ ህግ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር ስማቸውን አሻሽሎ ማምጣቱ በችሎቱ ተነቅፏል፡፡ አቃቢ ህግም ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ነገር ግን ለተከሳሹ ጥቅም ሲባል ተለዋጭ ቀጠሮ ከመስጠት ክሱን ማንበብ ተገቢ በመሆኑ በችሎቱ ክሳቸው ተነቦላቸዋል፡፡

እስከ ሰኔ 20/ 2011 ዓ.ም ድረስም መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡና አቃቢ ህግም ምላሽ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

በዚህ የክስ መዝገብ ከድር አብዲ እስማኤል የተባለ ግለሰብ የተያዘ ቢሆንም ስለስራ ድርሻው በክሱ የመንግስት የስራ ኃላፊ የሚል ቢሆንም፤ ግለሰቡ  ግን ገበሬ መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡

አቃቢ ህጉም ለችሎቱ  አቶ ከድር አብዲ እስማኤልን የሚፈልጋቸው ግለሰብ አለመሆናቸውን በማረጋገጡ፤ ችሎቱ በዛሬው ዕለት እንድለቀቅ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡