ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህን ተቀብለው አነጋገሩ

ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህን እና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊና የፕሬዝዳንቱ አማካሪ የሆኑትን የማነ ገ/አብ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

የኤርትራ ልዑካን በጠ/ሚሩ አባት ኅልፈት የተነሣ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የተሰማቸውን ኀዘን የገለጡ ሲሆን የሁለቱን ሀገራት የአንድ ዓመት የሰላም ጉዞ በተመለከተ ተወያይተዋል።

ሁለቱ ወገኖች ባለፈው አንድ ዓመት ግጭትን ለማስወገድ የተደረሰባቸውን ዋና ዋና ውጤቶች በማንሣት በቀጣይ ግንኙነቱን ለማጠናከር መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ተነጋግረዋል። ከሃያ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተገኘውን የኤርትራ የልኡካን ቡድን በመምራት በሀገራቱ መካከል የተካሄደውን ወሳኝ የሰላም ድርድር ያካሄዱት ኦስማን ሳሌህና የማነ ገ/አብ ነበሩ።

ይኽንኑ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ለመዘከርም ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ ከሁለቱ ባለ ሥልጣናት ጋር በመሆን የዛፍ ችግኝ በጠ/ሚር ጽ/ቤት ግቢ ተክለዋል።