በኢትዮ-ኬንያ ግንኑኝነት ላይ የሚመክር ዝግጅት በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ እንደሚዘጋጅ ተገለጸ

በኢትዮጵያና ኬንያ ግንኑኝነት ላይ የሚመክር ዝግጅት በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ፣ የኢኮኖሚያዊ እና ተዛማጅ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄድ የፓናል ውይይት አዘጋጅቷል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም እንዲሁም የናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግኑኝነት ጉዳይ ዳይሬክተር ዶክተር ጆይ ኪሩ ኦሪንዲ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ውይይት በሁለተኛው ግማሽ ምዕተ ዓመት የአገሮቹ ግኑኝነት የህዝብ ለህዝብ ትውውቅ እንዲኖር ወዳጅነቱ የበለጠ እንዲጠናክር በወጣቶችና ተማሪዎች ላይ ማተኮር ይገባዋል ብለዋል።

የናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የውይይት መድረኩን በማዘጋጀቱ አምባሳደር መለስ አመስግነው፣ የኬንያ ባንኮችና ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ባሳየችው አዲስ ለውጥ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

የናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የኮርፖሬት ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ጆን ኦሪንዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ኬንያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የዘለቀ የጠበቀና የማይዋዥቅ የመንግስታትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው፣ ይህንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ተቋማት ጋር ተባብረው መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያና ኬንያ ዙሪያ በተማሪዎች የሚደረጉ ጥናቶች እንደሚበረታቱ አመልክተው ዩኒቨርስቲው ተከታታይ የጋራ መድረኮችን ያዘጋጃል ብለዋል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ እና በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሁለቱ አገሮች ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነታቸውን የጀመሩበት 55ኛው ዓመት አስመልክቶ 500 የሚሆኑ ተሳታፊዎች የሚገኙበት የቢዝነስ ፎረም፣ የቢዝነስ መድረክ፣ የፎቶና የስዕል ኤግዚቢሽን መርሃግብሮች በኤምባሲው እና የኬንያ የንግድ ምክር ቤት እንደሚዘጋጁም ታውቋል።