ጠ/ሚ ዐቢይ ከጅቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍን ጋር ተወያዩ።

ሚኒስትሩ የፕሬዝዳንት እስማኤል ዑመር ጊሌን የኀዘን መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለማቅረብ ነው አዲስ አበባ የተገኙት። 

ከዚህም በተጨማሪ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም የኢኮኖሚ ትብብርን በማፋጠንና በማኅበራዊና ባሕላዊ ግንኙነቶች ላይ ተወያይተዋል።

ቀጠናዊ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮችን በተመለከተ በሱዳን መረጋጋትን ለማስፈን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አመራር ሥር የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት ኢጋድ ሚና ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ መክረዋል።

በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ለመዘከርም ሁለቱ ወገኖች በጽህፈት ቤቱ ግቢ ውስጥ ችግኝ መትከላቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡