ለሕዝብ ተቃውሞ መነሻ የሆኑ አሠራሮችንና ሕጎችን የማስተካከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ገለጹ

ለሕዝብ ተቃውሞ መነሻ የሆኑ አሠራሮችንና ሕጎችን የማስተካከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ገለጹ፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡

ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ ለሕዝብ ተቃውሞ መነሻ የሆኑ አመራሮችን መቀየር፣ የተቋማትን አደረጃጀትና አሠራር ማሻሻል፣ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እንደሆኑ በሪፖርታቸው አስታውቀዋል፡፡

ተቋማዊ ማሻሻያ በማድረግ በኩል በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርና ሌሎችም ተቋማዊ ማሻሻያ የተደረገባቸው መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከር አኳያም በእስልምና ሃይማኖቶች መካከል የነበረው መከፋፈል መጥበቡና በክልሎች መካከል የነበረው መካረር መርገቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡

ለወንጀልና ወንጀለኞች የማይመች ሀገርና ሕዝብ ለመፍጠርና ኃይልን በብቸኝነት መጠቀም የሚችል መንግሥት ለመፍጠር የሕዝብ ቅቡልነት ያላቸው ሕግጋትን ማዘጋጀት እንደሚገባ በማመን ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ተናግረዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ፣ የፀረ-ሽብር፣ የወንጀል፣ የመገናኝ ብዙኃን፣ የመረጃ ነፃነት፣ የንግድ፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ፣ የጦር መሣሪያ አጠቃቀምና አስተዳደር እና ሌሎችንም አዋጆች መሻሻላቸውንና በቀጣይም ሕጎችን የማሻሻል ሂደቶች እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡

ከ45 ሺህ በላይ ዜጎች በምሕረት አዋጅ ተጠቃሚ መሆናቸውን፤ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች በመላው ሀገሪቱ ከእስር መለቀቃቸውንና ከ260 በላይ የመገናኛ ብዙኃን ከእግድ መውጣታቸውንም በዓመታዊ ሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

ከሰሞኑ በአማራ ክልል መሪዎች እና በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ላይ የገጠመውን አደጋ በተመለከተም “ከለውጡ አተረፍኩኝ ከሚል ኃይል እንዲህ ዓይነት ፈተና አልጠበቅንም፤ ለውጡን ያመጡልን ጀግኖች ላይ መፈጸሙ ደግሞ ይልጥ አሳዛኝ ነው፡፡ ይህ ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ምርጥ ጓዶቻችንን መብላቱ መራር ሐዘን ሆኖብናል” ብለዋል፡፡

ጉዳዩን የሚያጣሩ የምርመራ ቡድኖች ተቋቁመው እየሠሩ መሆናቸውን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”የተሞከረው ድርጊት ስልጣንን ለመንጠቅ የተሞከረ መሆኑ፣ የጥቃቱ ዓላማ የተሰጠን ኃላፊነት ተጠቅሞ ስልጣን ለመያዝ የታለመ መሆኑ፣ መንግሥት ሕግ ለማስከበር፣ አጥፊዎችን ለመያዝ እየሠራ መሆኑንና በኢትዮጵያ ስልጣን ከእንግዲህ የሚያዘው በምርጫ ብቻ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል” ብለዋል፡፡