የኢትዮጵያን በአፍሪካ ሰላም የማስፈን ጥረት ደቡብ ኮሪያና ፊንላንድ እንደሚደግፉ ገለጹ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም ለማስፈን የምታደርገዉን ጥረት የደቡብ ኮሪያ እና የፊንላንድ መንግስታት እንደሚያደንቁና ድጋፍም እንደሚያደርጉ ገለጹ፡፡

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ እንዳርጋቸው የሁለቱን ሀገራት የወጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጽሕፈት ቤታቸው አነጋግረዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸዉን ሁለንተናዊ ግንኙነት እንደሚያጠናክሩ በመጠቆም፣ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችም መዋዕለንዋያቸዉን በኢትዮጵያ ለማፍሰስ ስምምነት አድርገዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካንግ ኪዩንግ ኋ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለችበትን የለውጥ ጎዳና ሀገራቸው ትደግፋለች ብለዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዘመናትን ያስቆጠረ እና በተለይም በኮሪያ በነበረው ጦርነት ውስጥ ኢትዮጵያዊያን የዋሉት አስተዋጽኦ የማይረሳ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ተገኝተው ጉብኝት ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው ሲሆን፣ በዚህም የመጀመሪያ ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ ማድረጋቸው የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡ አገራቸዉም ይህንን ግንኙነት ማጠናከር እንደምተፈልግ የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በሁለቱ ህዝቦች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ላይ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡  

በቀጣይም አገራቸው በኢንቨስትምንት ዘርፍ መሳተፍ ፍላጎት እንዳላት ጠቁመው፣ በተለይም በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሀገራቸው ባለሀብቶች መዋዕለንዋያቸዉን እንዲያፈሱ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን የለዉጥ ጎዳና ሀገራቸው አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደምታደርግ ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የፊን ላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሀቪስቶ ጋር በሁለቱ ሀገራት ጉዳይ ሰፊ ውይይት እና ስምምነት አድርገዋል፡፡

በዚህም የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በምትሰራቸው ስራዎች ዙሪያ ትኩረት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

በተለይም በቅርቡ በሱዳን የተፈጠረዉን አለመረጋጋት ሰላማዊ እንዲሆን ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያደረጉት ጥረት እንዲሁም ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋትን ለመፍጠር የምታደርገዉን ጥረት ሀገራቸው ፊንላንድ ታደንቃለች ማለታቸዉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

ለቀጠናዊ ሰላም ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት ሀገሪቷ አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸው፣ የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነትን ለማጠናከርም ሰፊ ስራ እንደሚሰሩ መግለፃቸዉን ቃለ አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡