የጨፌ ኦሮሚያ ከሐምሌ 7 ጀምሮ መደበኛ ጉባኤውን ያካሂዳል

የጨፌ ኦሮሚያ 10ኛ መደበኛ 4ኛ አመት 5ኛ የስራ ዘመን ስብሰባውን ከሐምሌ 7/2011 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 3 ቀናት በአዳማ ከተማ እንደሚያካሂድ የምክር ቤቱ አፌጉባኤ ሎሚ በዶ አስታወቁ፡፡

አፈጉባኤዋ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተመለከተው በጉባኤው የ2011 በጀት አመት አፈጻጸም እንደሚገመገምና ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ገልጸው፣ የክልሉ 2012 በጀትም ለምክር ቤቱ ቀርቦ እንደሚጸድቅ ተናግረዋል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎችም በሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ላይ እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል፡፡

የጨፌ ኦሮሚያ ባለፈው በጀት አመት በክልሉ መንግስት የተከናወኑ ስራዎችን ሁለት ጊዜ የገመገመ ሲሆን ከቀረቡለት 12 አዋጆች 10ሩን እንዲሁም ከሰባት ደንቦች ስድስቱን በማጽደቅ ወደ ስራ ማስገባቱን በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በበጀቱ ባካሄደው ክትትልና ቁጥጥር ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑን ጠቁመው፣ የበጀት አጠቃቀምና የኦዲት ግኝት ላይ በመመስረትም የገንዘብ ብክነትን የመቆጣጠርና የመንግስት ሀብትን የማስመለስ ስራ እንደተሰራም አስታውቀዋል፡፡

የህዝብ ቅሬታ አለባቸው በሚል በተለዩ ሁለት ከተማዎች ላይም አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አፈጉባኤ ሎሚ በዶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርተዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት አመት የህዝብ ምክር ቤቶችን አቅም የማሳደግ ስራ መከናወኑን የጠቆሙት አፈጉባኤዋ፣ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የክልሉ መንግስት ያስቀመጣቸው እቅዶች አፈጻጸሞችን በሚመለከት የህዝብ ውይይቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ እንደሀገር የተጀመረው ለውጥ እየገጠመው ያለውን ፈተና ለማለፍ ክልሉ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራና በፖለቲካው የተመዘገበውን ለውጥ በኢኮኖሚውም ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡