ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተወያዩ

በኤርትራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተወያዩ።

መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተከናወነ ያለውን ዘላቂ ሰላም የማስፈን ሂደትን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ነው የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገፃቸው ያስታወቁት።

በተጨማሪም የዛሬ ዓመት ሁለቱ ሀገራት በተፈራረሙት ባለ አምስት ነጥብ የሰላም እና የትብብር ስምምነት መሰረት ሁሉን አቀፍ ትብብር ማድረግ በሚችሉበት ዙሪያም ተወያይተዋል።

መሪዎቹ አዎንታዊ ለወጥ እየታየበት ያለውን የሀገራቱን ግኑኝነት እና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም የማስፈን ጥረትን የበለጠ ለማስፋት ተስማምተዋል።

በመጨረሻም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተመራው ልዑክ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በመሆን የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ነበር የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ አስመራ ያቀኑት።