በሶማሌ ክልል ከ3 ሺህ በላይ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ተያዘ

በሶማሌ ክልል በህገ ወጥ መንገድ በግለሰቦች እጅ የነበሩ ከ3 ሺህ በላይ የግልና የቡድን የጦር መሳሪያዎች በአሰሳ መያዙን የክልሉ ልዩ ፖሊስ ገለፀ ።

የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ኮማንደር ዘካሪያ አብዲ ለኢዜአ እንደገለፁት በህገ ወጥ መንገድ ተሰራጭተው በግለሰብ የጎሳ አባላት እጅ በብዛት የነበሩ የቡድንና የግል የጦር መሳሪያዎች ለግጭትና ለበርካታ ሰዎች ሀልፈት ምክንያት ሆኖ ቆይተዋል።

የክልሉ መንግስት በህገወጥ መንገድ ተሰራጭቶ በጎሳዎች እጅ የሚገኝ የጦር መሳሪያ እንዲሰበሰብ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ላለፉት ሦስት ወራት ተከታታይ አሰሳ ሲያደረግ ቆይቶ 3ሺህ 40 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን መያዙን ኮማንደሩ ተናግረዋል ።

ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች መካከል በግለሰብ ደረጃ መያዝ የማይገባቸው መካከለኛ የጦር መሳሪያዎች ፣ አውቶማቲክ ቀላል ጠብመንጃዎች ፣ ሽጉጦችና ቦምቦች ይገኙበታል ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቶጎ ውጫሌ የልዩ ፖሊስ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ዶላር መያዙንም ኮማንደሩ አክለው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።