ሰራዊቱ ከምንጊዜውም በላይ ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት በሚያስችለው ቁመና ላይ ነው

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከምንጊዜውም በላይ ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት በሚያስችለው ቁመና ላይ እንደሚገኝ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አደም ማህመድ ገለጹ።

በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ያተኮረ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ውይይት አካሂደዋል፡፡

የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አደም ማህመድ ውይይቱን ባስጀመሩበት ወቅት፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከምንጊዜውም በላይ ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት በሚያስችበት ቁመና ላይ እንደሚገኝም ነው ተናግረዋል፡፡

የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በቅርቡ በተቋሙ አመራሮችና በአማራ ክልል አመራሮች ላይ የደረሰው አደጋ ከፍተኛ ቁጭትን የፈጠረ መሆኑን በመግለጽ እና በማውገዝ በቀጣይ እንዳይደገም እንደሚሰሩ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ባወጡት ባለ 9 ነጥብ የአቋም መግለጫ አረጋግጠዋል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ለሃገራችን እና ህዝባችን ሰላም ሲባል መስዋዕትነት እየከፈለ የመጣ መሆኑን በመጥቀስ፥ በቀጣይም የተለያዩ ጽንፈኛ ኃይሎች እና ህገ ወጦችን በመታገል የሃገሪቱን ሰላም እና ደህንነት እንደሚያረጋግጥ ተገልጿል፡፡

የተሰው ጓዶች ህልፈት ተቋሙን ለቀጣይ ስራ የበለጠ ለመስዋዕትነትና ጀግንነት የሚያነሳሳ እንጅ የሚያዳክም እንዳልሆነ ሁሉም ሊገነዘበው እንደሚገባም ተቋሙ አስታውቋል፡፡

ውይይቱ ከምንጊዜውም በላይ ከፍተኛ መግባባትና የአንድነት መንፈስ የተፈጠረበት መድረክ መሆኑን ሚኒስቴሩ ለጣቢያችን የላከው መግለጫ ያመላክታል፡፡