አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ

የአማራ ክልል መደበኛ ጉባዔውን በዛሬው እለት መካሄድ ጀምሯል፡፡

ጉባዔው በመጀመሪያ ቀን መክፈቻው በሰኔ 15 ጥቃት ህይወታቸው ያለፈውን የቀድሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ህልፈት ተከትሎ የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት ለመተካት አቶ ተመስገን ጥሩነህን መርጧል፡፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን ብቸና ወይራ በምትባል ቀበሌ የተወለዱት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ላለፉት ዓመታት ከዝቅተኛ አመራር ጀምሮ እስከ ፌደራል ባሉ የስራ ኃላፊነቶች ክልሉንና ሀገሪቱን አገልግለዋል፡፡

በመከላከያ ሚኒስቴር፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የስትራቴጅ ዘርፍ፣ የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ፣ የአማራ ክልል ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው ከሰሩባቸው የስራ ዘርፎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአማራ ዲሞክራሲያ ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ዩሀንስ ቧያለው አቅራቢነት ዛሬ የተሾሙት አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ህዝብ አሁን ከገጠሙት ችግሮች በሳል አመራር እየሰጡ ህዝቡን እንዲያሻግሩ ጥሪ ቀርቧል ፡፡