አዲስ ወግ የውይይት መድረክ በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ነው

ሁለተኛው አዲስ ወግ የህዝብ ውይይት በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።

የብሔረ መንግሥት ግንባታዎች ውጣ ውረድ በኢትዮጵያ፣ ጦር የሰበቀና ሰላም ያነገበ የፖለቲካ አካሄድ ፍልስፍና በኢትዮጵያ በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ መነሻ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት ይደረግባቸዋል።

በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሀላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መሰል ውይይቶች ዜጎች መብታቸውን በስሜት ሳይሆን በሰከነ መንፈስ፣ በጉልበት ሳይሆን በእውቀት እንዲያቀርቡ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹና ግንዛቤን የሚያስጨብጡ ናቸው ብለዋል።

በየአደባባዩ እና መድረኩ መጣል ያለባቸው ሃሳቦች እንጂ ድንጋዮች መሆን የለባቸውም ነው ያሉት፡፡

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት  ኡባንግ ሜቶ በበኩላቸው ከብሄር በፊት ሀገር መቅደም እንዳለበትና በሀገር ግንባታ ላይም ሁሉም በጋራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ጥናታዊ ፅሁፎቹ በዶክተር ሰሚር ዩሱፍ፣ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ እና ዶክተር ኮንቴ ሙሳ የቀረቡ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እና አቶ ታምርአየሁ ወንድማገኝ ውይይቱን እየመሩት ይገኛል፡፡

በተጨማሪም  ብሔራዊ መግባባትን በማስፈን ሀገረ መንግሥት ግንባታን ለማሳለጥ የመንግሥታት ሚና በሚል ርዕስ፥ የመወያያ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ነው፡፡