የፈረንሳዩ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር አዲስ አበባ ገቡ

የፈረንሳዩ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ብሩኖ ለ ሜዬር ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ።

ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ጋር በአቪየሽን ዘርፍ በጋራ መስራት በሚቻልበት አግባብ ላይ መወያየታቸውን ከአየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

የሚኒስትሩ ጉብኝት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ከመንግስት ጋር የደረሱትን ስምምነት ገቢራዊ ማድረግ የሚቻልበትን አግባብ ለማመቻቸት ያለመ ነው።

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መጋቢት 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት፥ ሁለቱ ሃገራት በመከላከያ፣ በህዋ ሳይንስ፣ በኢኮኖሚና በሌሎችም ዘርፎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

ማክሮን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትንም የጎበኙ ሲሆን፥ ፈረንሳይ ለአብያተ ክርስቲያናቱ ጥገና እና ድጋፍ እንደምታደርግም መግለጻቸው ይታወሳል።