‹‹የአማራ እናት የመሪ መካን አለመሆኗን ለማብሰር በድጋሜ ከዚሁ ላይ ተገኝተናል›› አቶ ደመቀ መኮንን

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የአዴፓ ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንን በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ በዓለ ሲመት ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም ከአምስት ወራት በፊት በዚሁ ቦታ የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በዓለ ሲመት ላይ መታደማቸውን አስታውሰው ‹‹ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባልጠበቅነው ሁኔታ ወንድሞቻችን ተነጥቀን አንብተናል፤ ግን አንገታችንን ደፍተን አልቀረንም፤ የአማራ እናት የመሪ መካን አለመሆኗንም ለማብሰር በድጋሜ ከዚሁ ላይ ተገኝተናል›› ብለዋል፡፡ ዛሬም የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመሆን የጀመረውን ትግል በልጆቹ ሞት እንደማይቆም ለማሳየት ‹‹ሕይወት ይቀጥላልና እነሆ በአዲስ የሕይወት ጅማሮ ተነስተናል›› ነው ያሉት አቶ ደመቀ፡፡

ለመሪዎች የመሳሳት ዕድል ጭምር በመስጠት እየተከታተለ ትልልቅ ሐሳቦችን የሚለግስ ሕብረተሰብ እንደሚያስፈልጋቸው ያመለከቱት አቶ ደመቀ፣ መሪዎች የሚነሱትም የሚወድቁትም ከሕብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች በሚሰጥ ምላሽ በሚፈጠር የመርካትና ያለመርካት ሁኔታ በመሆኑ ሕብረተሰቡ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ሊያግዛቸው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ በታሪክ ሰንሰለት በርካታ ውጣ ውረዶችን እንደ ሀገር ማለፍ መቻሉን ያመለከቱት አቶ ደመቀ፣ ‹‹በፈታኝ ሁኔታ ሁሉ ሀቀኝነትና የሞራል ልዕልና አብረውን ነበሩ›› ብለዋል፡፡ የማኅበራዊ ጉዞ መነሻና መድረሻ ማኅበራዊ እሴት፣ የሞራል ልዕልናና ለእውነት መቆም መሆኑን በማመልከት የአማራ ሕዝብ ያጋጠመውን ከባድ ችግርና ኪሳራ ለመቀነስ እነዚህ የሞራል እሴቶቹ እንዳገዙት አመልክተዋል፤ እንዲጠበቁም አሳስበዋል፡፡

አሁን ላይ ከሩቅም ቢሆን እየታየ ያለው የሞራል እሴቶች መሸርሸርና ለእውነት ያለመቆም መሆኑን በማመልከት ሊታረም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ስለእውነት መቆምንና የሞራል እሴትን መጠበቅን ማስቀጠል እንደሚገባም መክረዋል፡፡ ‹‹እንደ ሀገር የዚህ ቀጠና ዝሆን ብንሆንም አንድም ሀገር ወረንም ተወረንም አናውቅም፤ ይህም የሞራል ልዕልናችን ማሳያ ነው፤ ይህንም ለትውልድ ልናሻጋግረው ይገባል፡፡

ጥላቻን፣ መገዳደልን፣ መጠፋፋትን በእንጭጩ ልንቀጨውና በእውነት አደባባይ ቆመን ልንፋረደው ይገባል›› ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፡፡ እኩልነት የሰፈነባት፣ ዴሞክራሲ ያበበባት ሀገር መገንባት እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ደመቀ ‹‹በአስቸጋሪና በአስጨናቂ ጊዜ የጨለማ ጊዜ ብርሃን፣ የለውጥ አቀጣጣይ መሪዎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው፤ ከእኛ በፊት የነበሩት በዚህ መልኩ ሀገር አስረክበውናል፡፡ ዛሬም ትናንት ያጣናቸውን መሪዎች በመተካት ግዴታ ውስጥ ሆነን ተተኪዎችን አምጥተናል›› በማለት የማኅበረሰባዊ እሴትን ቀጣይነት አመልክተዋል፡፡

አዲስ ርዕሰ መስተዳድር በመሆን የተተኩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው ከሕዝብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደፊት እንደሚዘልቁ እንደሚተማመኑባቸውም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የብርቱ አርሶ አደር ልጆች ስለሆኑና ባለፉት ዓመታትም የተፈተኑ ስለሆኑ በውጤታማነት እንደሚወጡት እተማመናለሁ፤ ለክልላችንና ለሀገራችን ዕድገት የቆማችሁ ሁሉ ከጎናቸው እንደትሰለፉ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ›› ነው ያሉት፡፡ ‹‹መደበኛ ሕይወት በተስፋ እንዲያንሰራራ በችግራችን ጊዜ ከጎናችን ለሆናችሁ የክልሎችና የፌዴራል መሪዎችና ሕዝቦችም አመሠግናለሁ›› ብለዋል፡፡ (ምንጭ፡- አብመድ)