የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ የክልል መሪዎች የአጋርነት መልዕክታቸውን አስተላለፉ

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ  የክልል መሪዎች የአጋርነት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በትላንትናው ዕለት የአማራ ክልል ምክር ቤት አቶ ተመስገን ጥሩነህን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አድርጎ የሾመ ሲሆን፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በበዓለ ሲመቱ ላይ ታድመዋል፡፡

በዚህም ማምሻውን ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት የአጋርነት መልዕክት ‹‹ኢትዮጵያውያን የሚያዋጣን ለጋራ አንድነታችንና ለልማታችን በጋራ መትጋት ነው፤ ፈተናዎች የጋራ ቤትን የሚያፈርሱ ከሆነ ማንም አይጠቀምበትም፤ የጋራ ቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ በአንድነት ልማቷን እና ሰላሟን አስጠብቆ ለማሻገር መትጋት ይገባል›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አንድነትና ቀጣይነት የማረጋገጥ ትልቅ ኃላፊነት መወጣት ተገቢ መሆኑንም አቶ ሽመልስ አሳስበዋል፡፡

የጥፋት መንገድ እንዳይደገም፣ ኢትዮጵያን ለዘመናት በአዙሪት ውስጥ ያኖራት በውይይትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ችግሮችን የመፍታት ችግር እንዲያበቃ ሁሉም በጋራ መታገል እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ሽመልስ፣ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ እና መንግስትም ከአማራ ክልል መንግስት ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ለሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች ተፈጻሚነት መንግስታቸው እንደሚሰራ ያረጋገጡት ደግሞ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መሰተዳደር አቶ ኡስማን ሙሃመድ ናቸው፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የተከሰተው ድርጊት የአማራን ሕዝብ ስም እና ታሪክ የማይመጥን እኩይ ተግባር በመሆኑ ሊወገዝ እንደሚገባው የገለጹት አቶ ኡስማን፣ ድርጊቱን የማይረሳ ነገር ግን ሊደገም የማይገባ መሆኑ ታውቆ የቆየ አንድነትን አጠናክሮ መሄድ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአፋር ክልል አጎራባች ከሆኑት ክልሎች መካከል ሰፊ የሆነ ቆዳ ስፋት የሚያዋስነው የአማራ ክልል ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ግንኙነቱም የተጠናከረ መሆኑን መስክረዋል፡፡ በአፋር ክልል አስካሁን በማንነቱ ማንም አለመፈናቀሉንና ወደፊትም ማንም ሊፈናቀልበት እንደማይችል አረጋግጠዋል፡፡

የነበረው ግንኙነቱም የበለጠ እንዲጠናከር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት፡፡ የሁለቱ ክልል ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ የቆየ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ግንኙነት ያላቸው በመሆናቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የበለጠ ሊጠናክር እንደሚገባም ጠይቀዋል፤ የአዴፓ አዲሱ አመራር የተፈጠረውን ክፍተት በመሙላት የተሰው አመራሮችን አደራ ከዳር ለማድረስ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአፋር ሕዝብ እና መንግስት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ለሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች እና ለሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች እንደ ቀድሞው ሁሉ ከጎኑ እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል፡፡

በሌላ በኩል የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርድን በድሪ ለርዕሰ መስተዳድሩ እና ለክልሉ መንግስት የአጋርነት መግለጫ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመልዕክታቸውም በሀረሪ ክልል የሚኖሩ የአማራ ብሔሮች መብታቸው ተጠብቆ፣ በአመራር ቦታዎችም እንዲሳተፉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ በመልካም አብሮነት የሚታወቅ መሆኑንም ገልጸው፣ መንግስታቸውም ከአማራ ክልል መንግስት ጎን እንደሚቆም ነው ያረጋገጡት፡፡፡

በበዓለ ሲመቱ የተገኙት የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ ዑመር ደግሞ ‹‹ለሀገራችን የሚጠቅማት በጋራ ሆኖ በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን መፍታት ነው፤ ለአማራ ክልል ሕዝብ ከዚህ ቀደም ችግር ላይ በወደቀበት ወቅት ከጎናቸው እንደቆምነው ሁሉ ወደፊትም ከጎናችሁ እንደምንቆም ለማረጋገጥ እወዳለሁ›› ብለዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብም ከአዲሱ ርዕሰ መስተዳድር ጎን እንዲቆምና እንዲያግዛቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፣ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ሕይወታቸው በማለፉ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፣ አዲስ ለተሸሙት ርዕሰ መስተዳድር ደግሞ የሥራ ዘመን ስኬትን ተመኝተዋል፡፡

በየደረጃው ያሉ መሪዎች ተቀራርበው እና በሰከነ መንገድ ተነጋግረው መስራት በሚያስፈልግበት ጊዜ የአማራ ብሔራዊ ክልል መድረኩን በማዘጋጀቱም ምስጋናም አቅርበዋል፡፡ ሀገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ እና ከለውጡ የሚገኘውን ተስፋ ለማጣጣምና የተንዣበቡ ፈተናዎችን በተባበረ ክንድ ለመመከት በጋራ መጋፈጥ ይገባል ብለዋል አቶ አሻድሊ፡፡

ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ምንም እንኳን የሚያሳዝን ቢሆንም፣ በትግል ሂደት የሚያጋጥም ፈተና በመሆኑ አንገት ሊያስደፋ እንደማይገባም ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹ይልቁንም ይበልጥ እልህና ቁጭት ውስጥ ሆነን የተጀመረውን ለውጥ የምናስቀጥልበት እና ሕዝብ የሚያነሳውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የምንመልስበት ነው›› ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

የአማራ እና የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስታት የጋራ ወሰን ያላቸው በመሆኑ ለጋራ ሕዝባቸው ጥቅም በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡ በተከሰተው ችግር ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች አሁን እየተመለሱ መሆናቸውን በመግለጽ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

ለአዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር መልካም የስራ ዘመን እንደሚሆን በመመኘት ወደፊት ከጎናቸው እንደሚሆኑም ቃል ገብተዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዑሞድ ኦጂሉም ለአማራ ክልል ሕዝብ ጥቅም ያለዕረፍት ሲሰሩ የነበሩ መሪዎች በማለፋቸው የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል፡፡ በበዓለ ሲመቱ ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ደግሞ በመንግሥታቸውና በሕዝቡ ስም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለአማራ ጥቅም እንታገላለን የሚሉ አካላት ሁሉ በጋራ በመንቀሳቀስ የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል ይኖርባዋል›› ያሉት አቶ ዑጂሉ ‹‹ኢትዮጵያውያን አንድነታችን ልቆ ሀገራችን ለአፍሪካ ምሳሌ እንድትሆን አክራሪ ብሔርተኝነትን መተውና ተባብሮ መሥራት ይገባናል›› ብለዋል፡፡

አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር መጭው ጊዜ ሕዝባቸውን በሠላም የሚያገለግሉበት እንዲሆንም በሕዝባቸውና በመንግሥታቸው ስም ተመኝተዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግስትም አጋርነታቸውን ለመግለጽ በባሕር ዳር ለተገኙት ርዕሰ መስተዳድሮችና ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች የባሕል አልባሳትና የጋቢ ስጦታ አበርክቷል፡፡

በትላንት ምሽት ምሽት በባሕር ዳር በተካሄደው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዓለ ሲመት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና አዴፓ ሊቀ መንበር ደመቀ መኮንን፣ የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮችና ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል፡፡

(ምንጭ፡- አብመድ)