መስዋዕት የሆኑ መሪዎችን ዓላማና ትግላቸውን ከግብ ማድረስ ይገባል – የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ትናንት ምሽት በበአለሲመታቸዉ ላይ ባደረጉት ንግግር “በዚህ የተደበላለቀ ስሜት ዉስጥ ሆነን በአንድ በኩል ሃዘናችንን በሌላ በኩል ደግሞ የማይቀረዉን የትግል ሽግግር የሆነዉን የአላማ ፅናትና ቁርጠኝነት አንግበን ስልጣን የተረከብንበት ጊዜ ነዉ” ብለዋል፡፡

በቅርቡ የተሰዉትን የክልሉን መሪዎች አስመልክተዉ ሲናሩም እነሱን ማጣት ከባድ ቢሆንም፤ ያለን አማረጭ የነሱን ዓላማ ማለትም ለህዝቦች ሰላምና ልማት የጀመሩትን ትግል ከግብ አድርሰን ህዝባችንን እነሱ በፈለጉት አቅጣጫ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ነዉ፡፡ በዚህ ላይ ከወደቅን ለሁለተኛ ሞት እንደገደልናቸዉ ስለሚቆጠር በዚህ ላይ ጠንክረን እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለተጎጂ ቤተሰቦች ዘላቂ ድጋፍ እንደሚደጉም ቃል ገብተዋል፡፡

ለክልሉ ህዝብ ባሰተላለፉት መልዕክትም ትግል ተሸጋጋሪና በየጊዜዉ አዳዲስ ክስተቶችን እንደሚያስተናግድ አስታዉሰዉ፤ አሁን የተደቀነብን ፈተና ቀላል ባይሆንም መሻገር ግን ይቻላል ብለዋል፡፡ ህዝቡ ከልማት ስራዉ በምንም ምክኒያት መደናቀፍ እንደሌለበትም ጠቁመዋል፡፡

የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን የክልሉ መንግስት ለማረም ዝግጁ መሆኑንና ለዚህም ህብረተሰቡ ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

“በየአካባቢዉ አላስፈላጊ ንግስና የተሰጣቸዉ ህገ ወጦችን እናስተካክላለን::”