የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤን ማካሄድ ጀመረ

የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 5ኛ የምርጫ ጊዜ 4ኛ የስራ ዘመን መደበኛ ጉባኤን ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ላክዴር ላክባክ በጉባዔው መክፈቻ እንደተናገሩት፤ ለህዝቦች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ሰላም ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ጥበብ በተሞላበት መንገድ መፍታት ይገባዋል፡፡

በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖችን በጋራ መታገል እንደሚገባም አፈጉባኤው አሳስበዋል፡፡

የ2011 ዓ.ም በጀት አመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈፃፀም በክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የቀረበ ሲሆን፤ አሁን ያለውን የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፉ ስራዎች ተሰርተዋል ተብሏል፡፡

አቶ ኡሞድ አያይዘውም የክልሉን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት በተደረገው ጥረትም በኤርትራ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ክልሉ መግባታቸውን አውስተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በሚኖረው የሁለት ቀናት ስብሰባ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የ2011 እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፤ የ2012 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት እንዲሁም ሌሎች አዋጆችንና ሹመቶችን መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በሚደረገው እንቅስቃሴ የምክር ቤት አባላት ህዝቡን በማስተባበርና አርአያ በመሆ እንዲሳተፉም ተጠይቋል። የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት በላከልን መረጃ መሰረት።