የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የኢጋድ ልኡካን ቡድንን ትናንት በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይቱ በኢጋድ-የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዶ/ር ኢስማዒል ዋዓይስ፣ የአርጄሜክ የጋራ ኮሚሽን ሊቀ-መንበር አምባሳደር ሌ/ጄነራል ኦጎስቲኖ እንዲሁም የሲቲሳም ተቀዳሚ ሊቀመንበር ሜጀር ጄነራል ደስታ አቢቸ ተገኝተዋል።
ውይይቱ በጁባ 67ኛው የኢጋድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ የተላለፉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮችና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ያተኮረ ነበር፡፡
የሰላም ሂደቱ አፈፃፀም ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የልኡካን ቡድኑ ለክቡር ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በቀጣይም የኢጋድ አባል ሀገራት በስምምነቱ መሰረት ለትግበራው አስፈላጊው እገዛና ድጋፍ እንዲያደርጉ የቡድኑ አባላት ጥሪ አቅርበዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ኢትዮጵያ በኢጋድ ሊቀመንበርነት ባላት ሚናና እንደጎረቤት ሀገርም ደቡብ ሱዳን ሰላም የሰፈነባት ሀገር እንድትሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡