የመከላከያ አባላት ያላቸውን የላቀ ስብዕና እና የአገር ፍቅር ለተተኪ ማስተላለፍ እንደሚገባቸው ተገለፀ

የመከላከያ አባላት ያላቸውን የላቀ ስብዕና እና የሀገር ፍቅር ለተተኪ ማስተላለፍ እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

የመከላከያ አዛዥነት ስታፍ ኮሌጅ ለ13ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 100 የሚሆኑ ከፍተኛ መኮንኖች ዛሬ በታላቁ ቤተ መንግስት አስመርቋል።

የመከላከያ አዛዥነት ስታፍ ኮሌጅ ዛሬ ካስመረቃቸው 100 ከፍተኛ መኮንኖች ውስጥ 92 ፖስት ስታፍ እና ስምንት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተከታተሉ ሲሆኑ 21 ተመራቂዎች ከጎረቤት አገሮች መሆናቸው ተገልጿል።

ኮሌጁ ዛሬ ካስመረቃቸው ተመራቂዎች የጎረቤት አገራት ጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን የተውጣጡ ከፍተኛ መኮንኖች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያ የሰጡት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድ የወታደር መኮንን መሆን ድርብ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ለተመራቂ የኢትዮጵያ መኮንኖች የአገሪቱን ታሪክ የህዝቦችን ባህል፣ ማንነትና ድንበር ጠንቅቀው በማወቅ የላቀ ስብዕናን በመገንባት ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የመከላከያ አባላት ያላቸውን የላቀ ስብዕና እና የአገር ፍቅር ስሜት ለተተኪ ማስተላለፍ እንደሚገባቸውም አክለዋል።

አባላቱ የፖለቲከኞች ሽኩቻ ሳይወስዳቸው ከወረዱ ዘረኞችና ደካሞች ጋር ሳይወርዱ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ለህዝቦች እኩልነትና ደህንነት እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በመጨረሻም መከላከያን የማዘመን ሥራ በሁሉም ተቋማቶች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለአብነትም ዘመናዊ ጀቶችና ሄሊኮፕተሮች፣ ሰው አልባ ሚሳኤል እና የሳይበር ስራዎች ላይ የማዘመን ስራ በፍጥነት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለመከላከያ አባላት የሚሰጠው ከስልጠና እስከ ትጥቅ የማዘመን ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተመራቂዎች ተረድተው ለቀጣይ አዳዲስ ስልጠና እና ትምህርት ራሳቸውን ዝግጁ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አደም መሀመድ በበኩላቸው መከላከያ የሰራዊቱን ተልዕኮ የመፈፀም አቅም እና ብቃት ለማሳደግ የሚያስችለው የሪፎርም ሥራ ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ከዚህ ውስጥ የመከላከያ አዛዥነት ስታፍ ኮሌጅ አንዱ በመሆኑ ዛሬ የተመረቁ ከፍተኛ መኮንኖች የተጀመረውን ተቋማዊ ሪፎርም ከግብ ለማድረስ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

ተመራቂ ከፍተኛ መኮንኖች በበኩላቸው የተሰጣቸውን ህገ መንግስታዊ ተልዕኮ ለመወጣት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆነው ለህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ዘብ እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

ተመራቂ ከፍተኛ መኮንኖቹ በኮሌጁ ያገኙትን የወታደራዊ ሳይንስና አመራር ተጠቅመው ህገ መንግስታዊ ግዳጆችን በስኬት ለማጠናቀቅ ያላቸውን ዝግጁነት ገልፀዋል።/ኢዜአ