በአዳማ ሲካሄድ የቆየው የደኢህዴን ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች መድረክ ተጠናቀቀ

በአዲስ አበባ የሚገኙ የደኢህዴን ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በአዳማ ያካሄዱት መድረክ ተጠናቋል፡፡

አመራሮቹ በደቡብ ክልል የክልል አደረጃጀት አስመልክቶ ይፋ በተደረገው ጥናት ላይ ተወያይተዋል፡፡

በደቡብ ክልል የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎችን ለመመለስ የተጠናዉ ጥናት የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብት የሚጥስ አለመሆኑም ተብራርቷል፡፡ 

የደኢህዴንና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ ደኢህዴን የህዝቦችን ጥያቄ በግምት ሳይሆን በእውቀት ላይ ተመስርቶ በጥናት ለመመለስ በ10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በመነሳት በሀገር ደረጃ አዲስ ልምድ ይዞ የመጣና አማራጭ ሃሳቦችን እያበረከተ የሚገኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የክልሉ 2011 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም የተገመገመ ሲሆን፤መድረኩ ብሄራዊና ሀገራዊ ማንነትን አጣጥሞ ለመሄድ መግባባት የተፈጠረበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ለአራት ቀናት በቆየው በዚህ መድረክ ከክልል አደረጃጀት ጥያቄ በተጨማሪ በወቅታዊ፣ አገራዊ፣ ክልላዊ እና በከተማው የፖለቲካዊና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር  አድርገዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ከ1 ሺህ በላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የድርጅቱ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡