ጠ/ሚ ዐቢይ በሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ሸንጎና የነፃነትና ለውጥ ኃይሎች መካከል በተደረገው የመጨረሻ የስምምነት ፊርማ ላይ ተገኙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ነሐሴ 11 ቀን 2011 ወደ ሱዳን ካርቱም በመጓዝ በወታደራዊ የሽግግር ሸንጎና በነፃነትና ለውጥ ኃይሎች መካከል የተደረገውን የመጨረሻውን የስምምነት ፊርማ ተከታተሉ::

ይህ የመጨረሻው ስምምነት ወታደራዊ ያልሆነ መንግስት ለመመስረት መንገድ ከፋች ነው ተብሏል::

ከስምምነት ፊርማው ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከነፃነትና ለውጥ ኃይሎች አባላት ጋር ተወያይተዋል:: አባላቱ ኢትዮጵያ ለዚህ ስምምነት መፈረም የተጫወተችውን ሚና በማድነቅ እነዚህ ሕገ መንግስታዊና ፖለቲካዊ ስምምነቶች ለዘላቂ ዴሞክራሲያዊና ልማት መሰረት ይጥላል ብለዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው፣ ይቅርታንና አንድነትን በመንከባከብ እንዲተጉ በማበረታታት ስኬታማ ውይይት መልካም መነሻ እንጂ ብዙ ስራ የሚጠይቀው መንገድ ከዚህ ቀጣዩ ነው ብለዋል::

ሴቶች በፖለቲካ አመራር ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ለዚህም አካታች እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተያያዘም የኢትዮጵያን ልምድ በማንሳት የነፃነትና የለውጥ ኃይሉ ይህንን 50-50 የፆታ አካታች ካቢኔ እንዲተገብሩ አስታውሰዋል::

በሱዳን ስምምነት ፊርማው ስነስርዓት በማስከተል ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሀገሪቱ በሚደረገው የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ወቅት የሱዳን ህዝቦች የሰላማቸውና የክብራቸው ተንከባካቢዎች እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል::

በሱዳን ጉዞአቸው ማብቂያም ከመቶ በላይ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወደሌላ ሀገር ለመሻገር ሱዳን የቀሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ይዘው ተመልሰዋል:: ከነዚህም ውስጥ በተለያየ ጥፋት እስር ቤት የነበሩም ይገኙበታል ነው የተባለው፡፡ መረጃው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ነው፡፡