በአቶ አብዲ መሐመድ ዑመር የክስ መዝገብ  የተከሰሱ ሰዎች ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ተወሰነ 

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት በቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሐመድ ዑመር የክስ መዝገብ ተጠቅሰው ያልተገኙ 11 ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ብይን ሰጠ።

በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው ሳይቀርቡ በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ ከተበየነባቸው ተከሳሾች የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ የነበሩት ጄኔራል አብዱራህማን አብዱላሂ፣ ሻለቃ ሼክ ሙክታር እና ሄጎ የተሰኘውን የአመፅ ቡድንን በምክትልነት ሲመሩ ነበር የተባሉት የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ መሐመድ አህመድ ይገኙበታል።

ችሎቱ ከነዚህ በተጨማሪ በክስ መዝገቡ የመኖሪያ አድራሻ ተፈልገው ያልተገኙ ሌሎች 7 ተከሳሾችም እንዲቀርቡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ እንዲደርሷቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በተሻሻለው ክስ ላይ 1ኛው ተከሳሽ የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ዑመር ከጠበቆች ጋር ተማክሬ የክስ መቃወሚያ አቀርላሁ ብለዋል።

ጉዳያቸውን በአካል እየተከታተሉ ከሚገኙ 14 ተከሳሾች የተፋጠነ ፍትሕ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም፤ ጉዳያችንን ፍርድ ቤቱ በትኩረት ይመልከትልን በማለት አመልክተዋል።

ችሎቱ የክስ መዝገቡ በጋራ የሚታይ በመሆኑ የተከሳሾች የግል አቤቱታ የክስ መቃወሚያ እና ከሌሎች መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የተጠቀሰውን ጊዜ ሊቆጠር ችሏል ብሏል፡፡