ወ/ሮ ሂሩት ዘመነ አዲስ አበባ ከሚኖሩ የኢጋድ አባል አገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሂሩት ዘመነ ዛሬ ነሀሴ 14 ቀን 2011 ዓም አዲስ አበባ ከሚኖሩ የኢጋድ አባል አገራት አምባሳደሮች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

የኢጋድ አባል አገራት አምባሳደሮች በቀጠናው ሰላምን በማስፈን ዘላቂ ልማት ለማስመዝገብ በሚደረገው እንቅሰቃሴ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።

አምባሳደሮቹ በበኩላቸዉ በቀጠናው በተለይም በደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፈን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከግብ እንዲደርስ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ  ውይይቱ በዋናነት የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ፈራሚ አካላት በነገው እለት በአዲስ አበባ ከሚያደርጉት ስብሰባ ጋር በተያያዘ ያለውን ቅድመ ዝግጅት ስራ በተመለከተ መረጃ መለዋወጥ ላይ ያተኮረ መሆኑን ነው የገለፁት።

በውይይቱ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የጅቡቲ፣ የኬንያ እና የኡጋንዳ አምባሳደሮች መሣተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።