ጳጉሜ ‘ጳጉሜን በመደመር’ በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ይታሰባል

‘ጳጉሜን በመደመር’ በሚል መሪ ሀሳብ ሀገራዊ የመርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የመደመር ስድስት ምሰሶዎችን ባማከለ መልኩ  ጳጉሜን በመደመር ሀገር አቀፍ መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ነው ፅህፈት ቤቱ ያስታወቀው፡፡
የተለያዩ የመንግስት አካላት የየዕለት እንቅስቃሴዎቹን ለማቀድ ፣ ለመምራት፣ ለማስተባበርና ለማስፈፀም ሀላፊነት ወስደው እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል እየፈፀሙ፡፡
በዚህም መሰረት  የጳጉሜን ስድስቱ ቀናት ስያሜ እና አስተባባሪዎች ይፋ የሆኑ ሲሆን ጳጉሜን 1 ብልፅግናን የወከለ ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስተባባሪነት፣ ጳጉሜን 2 ደግሞ የሰላም ቀን ሲሰኝ በሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፊሪያት ካሚል እንደሚመራ ነው የተገለፀው፡፡
ጳጉሜን 3 ሀገራዊ ኩራት የሚል ስያሜን ሲሰጠው በማስተባበር በኩል የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ሀላፊነቱን ወስደዋል፡፡
ጳጉሜን 4 ዲሞክራሲ የሚል ስያሜን በትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የተሰጠ ሲሆን ዕለቱን በአስተባባሪነት የሚመሩት ይሆናል፡፡
ጳጉሜን 5 የፍትህ ቀን ሆኖ እንዲታሰብና  የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ እንደሚያስተባብሩት ተመልክቷል፡፡
የመጨረሻው እና የአዲስ አመት ዋዜማው ጳጉሜን 6 ደግሞ የሀገራዊ አንድነት ቀን ሆኖ ታስቦ እንዲውል ውሳኔ ተላልፏል፡፡
ህብረተሰቡም በእነዚህ ቀናት ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ ወደ መጪው አዲስ አመት ተስፋን ሰንቆ ለመሻገር እንዲሰናዳ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ጥሪ አቅርቧል፡፡